በአክሱም የኤሌክትሪክ አገልግሎት በተደጋጋሚ መቆራረጥ በስራቸው ላይ ተጽእኖ እያሳደረባቸው መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በአክሱም የኤሌክትሪክ አገልግሎት በተደጋጋሚ መቆራረጥ በስራቸው ላይ ተጽእኖ እያሳደረባቸው መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ
አክሱም ሚያዝያ 15/2011 የኤሌክትሪክ መብራት አገልገሎት በተደጋጋሚ መቆራረጥ በስራችን ላይተጽእኖ እያሳደረብን ነው ሲሉ አንዳንድ የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ምሬታቸውን ገለጹ። የአገልግሎቱ በተደጋጋሚ መቆራረጥና ለቀናት የሚቆይበት ሁኔታ እንዲሻሻላቸውም ጠይቀዋል። በከተማው የዳቦ መጋገሪያ ባለቤት አቶ ሰሎሞን ፍሰሃ እንደተናገሩት የአገልግሎቱ በተደጋጋሚ መቆራረጥና ለተከታታይ ቀናት መጥፋት ለኪሳራ ዳርጓቸዋል። በዚህም በሳምንት እስከ ሁለት ኩንታል የተቦካ የዳቦ ሊጥ እንደተበላሸባቸው ተናግረዋል። አገልግሎቱ የሚቆራረጥበት ምክንያት አስቀድሞ ሊገለጽ ይገባል የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ሊፈለግ ይገባል ብለዋል። በሓወልቲ ቀበሌ በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ጥገና የተሰማራው ወጣት ክብሮም ዓለም በበኩሉ አገልግሎቱ ድንገት በመቋረጡ የአምስት ሺህ ብር ዋጋ ያለው ቴሌቪዥን በመቃጠሉ ለኪሳራ እንደተጋለጠ ይናገራል። ‘‘የኤሌክትሪክ ኃይል በምን እንደሚጠፋም አይታወቅም። ቅሬታ አለን።የሚጠፋበትና የሚለቀቅበት ሰዓት ታውቆ በፈረቃ ቢሆን ይመረጣል '' ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል። አገልግሎቱ በመቆራረጡ ምክንያት በስራችንና በገቢያችን ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ እየሳደረብን መጥቷል ነው ያለው ወጣቱ። የአገልግሎቱ መጥፋትና መቆራረጥ ስራቸውን ለመስራት እንዳላስቻላቸውና ገቢያቸውን እንደቀነሰባቸው የተናገሩት ደግሞ በከተማው የጸጉር ውበት ሳሎን ባለቤት ወይዘሮ መብርሂት ገብረህይወት ናቸው። በአገልግሎቱ መስተጓጎል በቀን እስከ 1 ሺህ 500 ብር የሚያገኙበትን ሥራ እንደሚያጡና ሥራ ፈተው ለመዋል መገደዳቸውን አስረድተዋል። ምግብ ለማብሰልና የዕለት ሥራቸውን ለማከናወን እንደሚቸገሩ የተናገሩት ደግሞ የማዕበል ቀበሌ ነዋሪ መምህርት አስካለ ተስፋጊዮርግስ ናቸው ። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአክሱም ዲስትሪክት አገልግሎት መስጫ ማዕከል ኃላፊ አቶ ዓብዱ በሪሁ ችግሩን አስመልክተው፣በከተማው አገልግሎቱ የሚቆራረጠው ከልማት መስፋፋት ስራዎች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የኤሌክትሪክ ምሶሰዎች በመኖራቸውና ያልተጠበቀ ኃይለኛ ዝናብም ለአገልግሎቱ መቆራረጥ ምክንያቶች እንደሆኑም ጠቅሰዋል። ከተማው የራሱ የሆነ የማከፋፈያ ማእከል/ሰብስቴሽን/ ስለሌለውም ችግር እንደገጠውም ገልጸዋል። ከአገልግሎቱ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚታዩትን ችግሮች ለማቃለል ያረጁ ምሶሰዎች የመቀየርና ሌሎች የቴክኒክ ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት 20 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ያለው የማከፋፈያ ጣቢያ/ሰብስቴሽን/ ግንባታ መከናወኑንና 15 ሺህ ቮልት በዓድዋና አክሱም ከተሞች እንደሚያሰራጭ ይታመናል ብለዋል።