ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ዥንፒንግ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ዥንፒንግ ጋር ተወያዩ
ሚያዚያ 16/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ዥንፒንግ ጋር ከቤልት ኤንድ ሮድ ጉባኤ በፊት የሁለትዮሽ ውይይት አካሄዱ:: ፕሬዚዳንት ዥንፒንግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር ያለፈውን አንድ ዓመት የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት እንደሚያደንቁ ገልፀው ቻይና ለኢትዮጵያ ዕድገት ትልቅ ቦታ ትሰጣለች ብለዋል:: በውይይቱ ወቅትም ፕሬዘዳንቱ እስከ ፈረንጆች 2018 ዓ.ም መጨረሻ የተጠራቀመ የብድር ወለድን ሙሉ በሙሉ እንደተሠረዘ አስታውቀዋል:: የቻይና መንግሥት የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክትን ጠቀሜታ ይረዳል ያሉት ፕሬዝዳንት ዥንፒንግ ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መንግሥታቸው እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የስትራቴጂ አጋርነት በማጠናከር እንደ አዲስ የጅቡቲ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ያሉ እዳዎችን ለመከለስ የሚረዱ ወሳኝ እንቅስቃሴዎችን ለመተግበር ያላትን ቁርጠኝነት ለፕሬዝዳንት ዥንፒንግ አስረድተዋል:: የባቡር ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ተሳታፊ የሆነችበት የቤልት ኤንድ ሮድ ማእቀፍ ቀዳሚ ውጤት መሆኑም ተገልጿል፡፡ ከአለም አቀፍ ቀጣናዊና ሁለትዮሽ መግባባቶች በተጨማሪ የወጣቷ ኢንጂነር ናዝራዊት አበራ እስርም እንዳሳሰባቸው መግለፃቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር በተለያዩ ዘርፎች አጠናክረው ለመቀጠልም ተስማምተዋል::