በባቡር መንገድ ፕሮጀክት ምክንያት ከይዞታቸው የተነሱ አርሶና አርብቶ አደሮች ቅሬታ ተገቢው ምላሽ ይሰጥ-የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም

አዲስ አበባ ሚያዝያ 15/2011 በአዋሽ ኮምቦልቻ ወልደያ፣ ሀራ ገበያ በሚዘረጋው የባቡር ፕሮጀክት ልማት ተነሽ አርሶ አደሮች ቅሬታ ዙሪያ ምርመራ በማድረግ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማቅረቡን የኢፌድሪ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡ ተቋሙ ምርመራውን ያደረገው በራስ ተነሳሽነት መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከአዋሽ ኮምቦልቻ ወልደያ፣ ሀራ ገበያ በሚያስገነባው የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት ከአማራ ክልል የተነሱ በርካታ አርሶ አደሮች ከካሳ አከፋፈል፣ ከጎርፍ መፋሰሻ፣ ከመተላለፊያ መንገድ፣ ከመልሶ ማቋቋምና ልማት ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ የአስተዳደር በደል ተፈፅሞብናል በሚል በተደጋጋሚ ለተቋሙ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ በዚህም ተቋሙ ምርመራ ያደረገው ቅሬታዎችን መነሻ በማድረግ ነው ብሏል፡፡ በመሆኑም በተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 211/92 አንቀጽ 24/2 መሠረት በራስ ተነሳሽነት ምርመራውን ለማካሄድ እንደ በቂ መነሻ ምክንያት ተደርጎ መወሰዱንም ጠቁሟል፡፡ ከፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ ከይዞታቸው የተነሱ አርሶአደሮች ያሉባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ወይም የአስተዳደር ጥፋቶችን አጣርቶ ተገቢውን የመፍትሔ ሀሳብ ለማቅረብ ምርመራ ማካሄዱንም ገልጿል፡፡ በተካሄደው ምርመራም በርካታ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በፕሮጀክቱ ምክንያት ይዞታቸው የተወሰደባቸው መሆኑንና የአስተዳደር በደል የደረሰባቸው መሆኑን ከወረዳና ከተማ አስተዳደሮች በተገኘው መረጃ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ተቋሙም በአዋጅ ቁጥር 211/92 አንቀጽ 26/3 መሠረት የምርመራውን ግኝት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይመለከታቸዋል ለሚባሉት ለኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና ለአማራ ክልል አስተዳደር ምክር ቤት የመፍትሄ ሀሳቦችን በዝርዝር አቅርቧል፡፡ ፕሮጀክቱ ስላለው አገራዊ የልማት ፋይዳና ጥቅም በቂ የሕዝብ ውይይት ግንዛቤ ሊፈጠር እንደሚገባ፣ ኮርፖሬሽኑ ወደፊት ለሚገነባቸው የባቡር ፕሮጀክቶች ይዞታቸውን እንዲለቁ ለሚደረጉ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባልም ብሏል፡፡ እንዲሁም የኑሮ ደረጃቸው ከቀድሞው የተሻለ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል አግባብነት ያለውና ውጤታማ የሆነ የካሳ ክፍያና የመልሶ የማቋቋም ፓኬጅ ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ ለኮርፖሬሽኑ ከተሰጡ የመፍትሔ ሀሳቦች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው ብሏል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ለይዞታቸውና ለንብረታቸው ተገቢው ካሳ ያልተከፈላቸው አርሶ አደሮችን በመለየትና የካሳ ስሌቱን በመወሰን ለኮርፖሬሽኑ በማቅረብ ተገቢው ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል ሲልም ተቋሙ ጠቁሟል፡፡ እንዲሁም በከተማ ውስጥ ቤታቸው ለፈረሰባቸው ሰዎች ምትክ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል በማለት በተቋሙ አዋጅ ቁጥር 211/92 አንቀፅ 26/3 መሠረት ምርመራውን ያካሄደው ቡድን ለአማራ ክልል አስተዳደር ምክር ቤት የመፍትሔ ሃሳብ ማቅረቡን ተቋሙ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም