ቀጥታ፡

በሚቀጥለው ሳምንት ሦስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ሊመረቁ ነው

ሚያዝያ 15/2011 በሚቀጥለው ሳምንት ሦስት የመስኖ ፕሮጀክቶች እንደሚመረቁ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተሰሩ ስራዎች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። ሚኒስቴሩ የመስኖ ልማትን በማስፋፋትና አገሪቷን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ዘመናዊ የመስኖ ልማት ተግባራትን ገቢራዊ የማድረግ ግብ ጥሎ እየተንቀሳቀሰ ነው። ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ፣ የተሟላ የመስኖ ልማት መሪ እቅድ ማዘጋጀት፣ የተቀናጀ የዲዛይን፣ የግንባታና የቁጥጥር ስርዓት ማውጣትና በመስኖ ልማት የስራ ዕድል መፍጠር ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል። ሚኒስትር ደኤታው ዶክተር አብርሃ አዱኛ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በአገሪቷ እስከ 2010 ዓ.ም መጨረሻ የነበሩ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በመገምገምና መነሻ በማድረግ ሲሰራ ቆይቷል። እንደ ዶክተር አብርሃ ገለጻ፤ በተያዘው ዓመት 51 ሺህ 600 በላይ  ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ዕቅዱን ለማሳካት የሚረዱ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። እስከ አሁንም በአማራ ክልል የርብ እንዲሁም የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች በጋራ የሚጠቀሙበት የጊዳቦ ግድቦች መመረቃቸውን አስታውሰዋል። በሚቀጥለው ሳምንትም በተመሳሳይ ሦስት የመስኖ ፕሮጀክቶች እንደሚመረቁ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል። በአማራ ክልል የተገነባው የመገጭ ሰራባ የመስኖ ፕሮጀክት ከሚመረቁት መካከል አንዱ ሲሆን ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸዋል። 4 ሺህ ሄክታር ለማልማት ያስችላል ተብሎ የተገመተው ፕሮጀክቱ ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መሆኑን አመልክተዋል። ፕሮጀክቱ ቀድሞ የተጠናቀቀ ቢሆንም በኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር ወደ ሥራ ሳይገባ መቆየቱንና በአሁኑ ወቅት ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ችግሩ እየተፈታ በመሆኑ ስራ ለማስጀመር ተወስኗል ነው ያሉት። ዶክተር አብርሃ እንደሚሉት፤ በኦሮሚያ ክልል አደአ ወረዳ የሚገኘው የአድአ በቾ ፕሮጀክት ባለፈው ዓመት የተጠናቀቀ ቢሆንም የሚረከብ አካል ባለመገኘቱ ሳይተላለፍ ቆይቷል። ''አሁን ላይ ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ እንዲተዳደር ተወስኗል'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ውጤታማነቱ በ600 የውሃ ማስተላለፊያ ቦዮች ላይ ሙከራ ተደርጎ በመረጋገጡ ይመረቃል። በኦሮሚያ ክልል የመቂ ዝዋይ የመስኖ ፕሮጀክት 4 ሺህ ሄክታር የሚያለማ እንደሆነ ጠቁመው የመጀመሪያ ምዕራፍ 2 ሺህ ሄክታር የሚያለማው በተመሳሳይ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚመረቅ ጠቁመዋል። 80 ሺህ ሄክታር የሚያለማው የአርጆ ግድብ 66 በመቶ ግንባታው መጠናቀቁንና ለስኳር ልማትና ለማህበረሰብ ግልጋሎት እንዲውል ታስቦ እየተገነባ እንደሆነም አስረድተዋል። ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የሚከፈለው የካሳ ጉዳይና የጸጥታ ችግሮች ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ደረጃ እንዳይፋጠኑ ምክንያቶች መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል። በመስኖ ዘርፍ የስራ ዕድል ፈጠራ ለ12 ሺህ ወጣቶች ስራ በመፍጠር 50 ሺህ ሄክታር እንዲያለሙ ግብ ተይዞ እንደነበርና ከክልሎች ጋር በመነጋገር እስካሁን 34 ሺህ ሄክታር የሚለማ መሬት መገኘቱን ተናግረዋል። በሌላ በኩል በኃይል መስክ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እንደተከናወኑ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና ገልጸዋል። በዳቡስ ወንዝ ከ300 እስከ 350 ሜጋ ዋት ኃይል እና ከዋቤ ወንዝ ደግሞ ከ100 እስከ 150 ሜጋ ዋት ሊደርስ የሚችል ኃይል ለማመንጨት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በገጠር አካባቢ የባዮ ጋዝ ተደራሽነትን ለማሳደግ የባዮ ጋዝ ማብላያዎችን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑንና 50 በመቶ መሳካቱንም ዶክተር ፍሬህይወት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ከ5ሺ700 በላይ የባዮ ጋዝ ማብላያዎችን ለመገንባት ታቅዶ ግማሽ ያህሉን መገንባት ተችሏል። የኤሌክትሪክ መስመር የማይደርስባቸውን የገጠር አካባቢዎች የፀሀይ ኃይል እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ፍሬህይወት በ2011 ዓ.ም 15 ሺህ የፀሀይ ኃይል ቴክኖሎጂዎችን ለማሰራጨት የተያዘው እቅድ 40 በመቶ መሳካቱን ጠቁመዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም