በጎንደር የሸማቾችን መብትና ደህነነት ለማስጠበቅ የሚረዳ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ክትትል እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር የሸማቾችን መብትና ደህነነት ለማስጠበቅ የሚረዳ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ክትትል እያደረገ ነው
ሚያዝያ 15/2011 የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የሸማቾችን መብትና ደህነነት ለማስጠበቅ የሚረዳ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ክትትል እያደረገ መሆኑን የጎንደር ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መመሪያ አስታወቀ፡፡ የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ደሴ አለባቸው ለኢዜአ እንዳሉት በበዓሉ ምክንያት በማንኛውም የፍጆታ ምርቶችና እቃዎች ላይ ጭማሪ እንዳይኖር ጭምር ነው የግብረ ኃይሉ ክትትል፡፡ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ ከማድረግ ባለፈ በአንዳንድ ምርቶች ላይ በተለይም በቅቤና ማር ላይ ባዕድ ነገር እንዳይጨመርም ትኩረት ተስጥቷል፡፡ በክፍለ ከተማ ጭምር የተቋቋመው ግብረ ኃይል በእያንዳንዱ የገበያ ቦታና ንግድ ድርጅት ቁጥጥሩን በመቀጠል ሁሉም የንግድ ተቋማት የዋጋ ዝርዝር እንዲለጥፍ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በመንግስት ድጎማ የሚገቡ መሰረታዊ ምርቶችን በመምሪያው በኩል እንዲሟሉና በአግባቡ እንዲሰራጩ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደሴ እስካሁን በተደረገ ጥረትም የአቅርቦት እጥረት አለመኖሩን ገልጸዋል። "ባዕድ ነገር የመጨመርና የተጋነነ ዋጋ ጭማሪ አልታየም "ያሉት ምክትል ኃላፊው እስካሁንም 48 ምግብና ምግብ ነክ ምርት አቅራቢ ድርጅቶች ላይ ክትትል መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በተደረገው ክትትልም አምስት ዘይት መጭመቂያ ቤቶችና ሦስት ዱቄት ፋብሪካዎች የንፅህና ጉድለት ተገኝቶባቸው እንዲታሸጉ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ከከተማው ሸማቾች መካከል ወይዘሮ ትዕግስት በላይ በሰጡት አስተያየት ከአትክልት በስተቀር እስካሁን በሌለው ምርት የዋጋ ጭማሪም ሆነ የአቅርቦት እጥረት እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል፡፡ የዋጋ ጭማሬ እንዳይኖር መንግስት አሁን እያደረገ ያለውን ክትትል አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚፈልጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው ሸማች አቶ መለሰ ጥላሁን ናቸው፡፡ በእህል ንግድ የተሰማሩት አቶ አባይ ወረታው በበኩላቸው እስካሁን የአቅርቦት ችግር ባለመኖሩ የዋጋ ጭማሪ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡