ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች መንግስት ህዝቦችን የማቀራረብ ተግባር እንዲያከናውን ተጠየቀ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 15/2011 መንግሥት በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የተፈጠረውን ጊዚያዊ ግጭት አስወግዶ ሠላም እንዲያሰፍንና "የቀድሞ ግንኙነታችንን እንድናድስ የማቀራረቡን ሥራ ትኩረት ሰጥቶ ይሥራልን" ሲሉ ግጭት የተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ጠየቁ። ግጭቱን ለመፍታት የተቋቋመው የጸጥታ ምክር ቤት በበኩሉ፤ የአካባቢውን ጸጥታ ለማስጠበቅና የሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች ግንኙነት ወደቀድሞ ቦታው ለመመለስ በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ የአጣዬ፣ የካራ ቆሬ፣ የቆሬ ሜዳና የማጀቴ ንዑስ ወረዳ እና በአማራ ክልል በኦሮሞ አስተዳደር ልዩ ዞን የደዌ ሐራ አካባቢ ከመጋቢት 27 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መንስኤው ባልታወቀ ምክንያት በተቀሰቀሰ ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ በርካቶች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የጋዜጠኞች ቡድን ግጭቶቹ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመገኘት ጉዳት የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተዘዋውሮ አነጋግሯል። በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ የአጣዬ፣ የካራ ቆሬ፣ የቆሬ ሜዳና የማጀቴ ንዑስ ወረዳ እና በአማራ ክልል በኦሮሞ አስተዳደር ልዩ ዞን ከሚሴና የደዌ ሐራ ወረዳ የሃይማኖት አባቶች፣ነዋሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በግጭቱ ልጆቻቸው ሞተዋል፣ ንበረታቸው ወድሟል ቀሪው ደግሞ ተዘርፏል። በተለይም የኤፍራታና ግድም ወረዳ የአጣዬ፣ የካራ ቆሬ፣ የቆሬ ሜዳና የማጀቴ ንዑስ ወረዳ ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሎዎችና የሃይማኖት አባቶች እንደተናገሩት፤ ግጭቱ የተጀመረው ከመጋቢት 27 ቀን 2011 ዓ.ም ዓርብ ጀምሮ ይሁን እንጂ የሰው ሕይወት የቀጠፈውና ደም አፋሳሽ ግጭት የተካሄደው እሁድ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ነው። "ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ወንድሞቻችን ጋር ከዚህ በፊት በግጦሽ መሬትና ከብቶች ድንበር አልፈው ሰብል ሲያበላሹ የሀገር ሽማግሌዎች የሚፈቱት መጠነኛ ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበር" ነዋሪዎቹ ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት በነበሩ ግጭቶች ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ በታጠቀና በተደራጀ ሃይል ለሦስት ቀናት ግጭት በመፈጠሩና መንግሥት በፍጥነት ባለመድረሱ በሁለቱም ወንድማማች ወገኖች መካከል የሰው ሕይወት ማለፉና ንብረት መውደሙ እንዳሳዘናቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ በጋብቻ የተሳሰረ፣ በሀዘንም ሆነ በደስታ የማይለያይ ነው ያሉት የግጭቱ ተጎጂዎች መንግሥት የቀደመውን የሁለቱን ማኅበረሰቦች ሠላም በመመለስ እርቅ የማውረድ ሂደቱን በፍጥነት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል። "አሁንም እኛ በሃይማኖታችን ሠላምን እየቀሰቀስን ነው፤ ግጭትና ደም መፋሰስ ይብቃ የሚያዋጣን ሠላም ነው እያልን ነው" ያሉት መልአከ ምህረት ፍሰሃ አስፋው ናቸው ፡፡ ግጭት በተከሰተባቸው በአንዳንድ የአማራና የኦሮሞ ማኅበረሰብ በሚኖሩባቸው አዋሳኝ ቀበሌዎች የሚኖሩ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል በተነሳሽነት የእርቅ ሂደት መጀመሩንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። በአማራ ክልል በኦሮሞ አስተዳደር ልዩ ዞን ከሚሴ እና በልዩ ዞኑ የደዌ ሐራ ወረዳ ነዋሪዎች፣የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው፤ የሁለቱን ሕዝቦች በማጋጨት ለማለያየት ጣልቃ የሚገቡ የጥፋት ሃይሎች እንዳሉ ተናግረዋል። ይሄም ግጭት በነዚህ የጥፋት ሃይሎች የተቀነባበረ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ መንግሥት እነዚህን የጥፋት ሃይሎች ከሕዝብ ጋር በመተባበርና በመለየት ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቀው፤ የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ በደም የተሳሰረ በመሆኑ በማንም የጥፋት ሃይሎች አንለያይም ብለዋል። የከሚሴ ዞን ነዋሪ መሃመድ የሱፍ በበኩላቸው "እኛ እዚህ ካሉ የአማራ ወንድሞቻችን ዛሬም ነገም ወደፊትም አብረን ነን፤ ዛሬ በጎራዴ ለሁለት እንኳን ቢከፍሉን አንከፈልም አንድ ነን እኛ፤ አሁንም ቢሆን ይሄ ብጥብጥ እንዴት ተነሳ ለምትሉት እያንዳንዱ የሀገር ሽማግሌ ያውቀዋል። ብጥብጡ ልማታችን ላይ የመጣ ብጥብጥ ነው።" ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማስቆምና የአካባቢውን ሠላም ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ግጭቱ የተከሰተባቸው ዞን፣ ከፌዴራል ፖሊስና መከላከያ በተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎች በጥምር የተቋቋመው የጸጥታ ምክር ቤት ሰብሳቢዎቹ እንደተናገሩት፤ ግጭት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች የጸጥታ ኃይሎችን በማሰማራት አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ተደርጓል። ቅድሚያ ተሰጥቶት የተሠራው አካባቢውን ማረጋጋት ነው ያሉት የምክር ቤቱ ሰብሳቢዎች፤ አንጻራዊ ሠላም በመስፈኑም የትራንስፖርት እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን የማስጀመር ሥራ መሰራቱንም አስረድተዋል። በቀጣይም የሕዝቡን ወንድማማችነት ለመመለስ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋበሩን እንዲቀጥል ለማድረግ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቶች የተጀመሩ ሲሆን፤ ሕዝቡን የማቀራረቡም ሥራ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ታየ እንዳሉት "የሕዝብ  ለሕዝብ ግንኙነቱ መቋረጥ የለበትም ፤ የተያዙ መድረኮች አሉ ሕዝብ ለሕዝብ ቀርቦ የሚነጋገርበት፤ ሕዝቡ ሲቀራረብ ደግሞ ወንጀለኛንም ለመያዝ ያስችላል ይሄን እኛም አበክረን እየሠራን ነው።" ብለዋል፡፡ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ተዘዋውሮ የተመለከተው የኢዜአ የጋዜጠኞች ቡድን የሕዝብ ትራንስፖርት እና እንደ ቴሌ፣ ባንክና የህክምና ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ተከፍተው አገልግሎት ሲሰጡ ተመልክቷል። ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቶች አሁንም ዝግ መሆናቸውንም ተመልክቷል። ጥምር የጸጥታው ምክር ቤት መንሴውን እያጣራሁ ነው በሚለው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱ፣ ንብረት መውደሙና ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው መዘገቡ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም