ከኤርትራ ጋር የተጀመረውን የንግድ ግንኙነት ሕጋዊ መሥመር ለማስያዝ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ተደራጅተዋል-- የጉምሩክ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ከኤርትራ ጋር የተጀመረውን የንግድ ግንኙነት ሕጋዊ መሥመር ለማስያዝ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ተደራጅተዋል-- የጉምሩክ ኮሚሽን
መቐለ ሚያዝያ 15/2011 ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የጀመረችው የንግድ ግንኙነት ሕጋዊ መሥመር ለማስያዝ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች መደራጀታቸውን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ። የዛላአንበሳና የራማ ከተሞች ነዋሪዎችና ባለሃብቶች ሥራው ለህዝብና ለአገር የጎላ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የመቐለ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ምህረተአብ ገብረ መድህን ለኢዜአ እንደገለጹት የአገሮቹን ገቢና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴ ሕጋዊ የሚያደርጉ ተግባራት ተከናውነዋል። ከሥራዎቹ መካከልም ህንፃዎችን የማስተካከል፣የሰው ኃይል እንደገና የማደራጀትና የውስጥ ቁሳቁስ ማሟላት ይገኙበታል። የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የመለየትና ተጨማሪ መክፈትም ሌላው ሥራ ነበር ያሉት አቶ ምሕረተአብ ፣ ከዚህ ቀደም በሑመራ ከነበሩት ሶስት የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ተጨማሪ ሶስት አዳዲስ ጣቢያዎችን መከፈታቸውን አስረድተዋል። ተጨማሪ የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች መከፈት በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ይወጡ የነበሩት የአገር ውስጥ ምርቶችን ለመቆጣጠር ተጨማሪ አቅም መፍጠር መሆኑንም ነው ሥራ አስኪያጁ ያመለከቱት። የዛላአንበሳና የራማ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችም ወደ ሥራ የሚገቡበት አደረጃጀት መፈጠሩንም አመልክተዋል። የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥትና የየአካባቢው መስተዳድሮችም ኮሚሽኑ የሚገለገልባቸው ህንፃዎች እንዲያገኝ ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ምህረተአብ ገልጸዋል። በትግራይ ማእከላዊ ዞን በራማ ከተማ የህዝብ አገልግሎት ይሰጥበት የነበረው አንድ ህንፃ ለጉምሩክ መሰጠቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል። በአካባቢውየጉምሩክ አገልግሎት የሚጀምርበት ዋነኛ ዓላማም የአገሮቹን የገቢና ወጪ ንግድን ሕጋዊ በማድረግ የመንግሥትን ገቢን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል። በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በዛላአንበሳ ከተማና አካባቢው የሚንቀሳቀሱት ባለሃብት አቶ የማነ ኢዮብ እንዳሉትም ፣ በዛላአንበሳ ከተማ የጉምሩክ አገልግሎት መጀመር ጠቀሜታው በርካታ ነው። ከዛላአንበሳ ወደ ምፅዋ ወደብ ያለው ርቀት 260 ኪሎ ሜትር ብቻ በመሆኑ የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ ጠቄሜታ አለው ብለዋል። አቶ ጣዕመ ለምለም የተባሉት ሌላው የዛላአንበሳ ከተማ ነዋሪና የሆቴል ባለቤት በበኩላቸው፣በሁለቱ አገሮች መካከል የሚኖረው የሰውም ሆነ የንብረት እንቅስቃሴ በህጋዊ መንገድ እንዲሆን ጉምሩክ ወሳኝ ነው ይላሉ። ‘‘በአካባቢያቸው የጉምሩክ አገልግሎት እንዲኖር ማድረግ ህጋዊ አሰራርን በማጎልበት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው ያጎላዋል‘‘ ያሉት ደግሞ በትግራይ ማእከላዊ ዞን የራማ ከተማ ነዋሪ አቶ ታደሰ ወልደገብርኤል ናቸው።