ቀጥታ፡

ዜጎችን በውጭ አገራት ስራ እንዲያስቀጥሩ ለማንም አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅት የድጋፍ ደብዳቤ አለመጻፉ ተገለጸ

ሚያዝያ 15/2011 ለተለያዩ አገራት ዜጎችን ስራ እንዲያስቀጥሩ ለየትኛውም አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅት የድጋፍ ደብዳቤ እንዳልጻፈ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ ሚኒስቴሩ ይህንን የገለጸው የኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅትበተለ ያዩ አገራት ስራ ለማስቀጠር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  የድጋፍ ደብዳቤ አግኝተናል  በሚል መሰራጨቱን ተከትሎ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ደብዳቤው የሃላፊ ፊርማ የሌለውና ፍጹም ሀሰት እንደሆነ ገልጸው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጻፈ የተባለውን ደብዳቤ ማን እንዳሰራጨው ሚኒስቴሩ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ለኢዜአ ገልጸዋል። ዜጎችም ደብዳቤው የሚኒስቴሩ እንዳልሆነ ሊያውቁ እንደሚገባና ሀሰት በሆነው ደብዳቤ ተነሳስተው ችግር ውስጥ እንዳይገቡ እንዲሁም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ አገራት ዜጎችን ስራ እንዲያስቀጥሩ ለማንም አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅት የድጋፍ ደብዳቤ እንዳልጻፈና ሚኒስቴሩ ይህን መሰል ወንጀል የሚፈጽሙ ተቋማትን ተከታትሎ ለህግ እንደሚያቀርብም አመልክተዋል። በማህበራዊ ሚዲያዎች በተሰራጨው ደብዳቤም የኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅት ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠውን እውቅና በማያያዝ እየሰራ እንደሚገኝና ድርጅቱ እየሰራሁባቸው ያሉ አገራት ስም ዝርዝር ይጻፍልኝ ብሎ ድርጅቱ መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም ለሚኒስቴሩ ባመለከተው መሰረት ህጋዊ ሆኖ እየሰራባቸው ያሉ አገራት ዝርዝር አስቀምጠናል ይላል። በምድብ አንድ የኬይማን ደሴቶች፣ ካናዳ፣ ቻይና፣ ታይላንድ፣ ሲንጋፖር፣ ካምቦዲያ አውስትራሊያ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኔፓል፣ አሜሪካ እና ህንድ፤ በምድብ ሁለት ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ አየርላንድ፣ ፊንላንድ፣ ቱርክ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ፖላንድ፣ ዴንማርክ፣ ስዊዘርላንድ፣ ኒውዝላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ቤልጂየም፣ ኦስትሪያ፣ አይስላንድ፣ ኖርዌይና ሉክሰምበርግ ድርጅቱ ህጋዊ ሆኖ የሚሰራባቸው አገራት እንደሆነ በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው ደብዳቤ ያሳያል። በደብዳቤው ላይ ማንኛውም ለስራም ሆነ ለጉብኝት ከኢትዮጵያ የሚወጡ ዜጎች የተጠቀሱትን አገራትን በህጋዊነት እየሰራ ከሚገኘው የኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅት ብቻ አገልግሎትን ማግኘት እንደሚቻልና በህገወጥ መንገድ ተታላችሁ ላልተፈለገ እንግልት እንዳትዳረጉ የሚል መልዕክትም አለው። በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው ይህ ደብዳቤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳልጻፈና ፍጹም ሀሰት እንደሆነ በመግለጽ ዜጎች በሀሰት ደብዳቤ እንዳይዘናጉ ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም