በሚቀጥሉት አስር ቀናት በርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ዝናብ ያገኛሉ - ብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ ኤጀንሲ - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት በርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ዝናብ ያገኛሉ - ብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ ኤጀንሲ
አዲስ አበባ ግንቦት 27/2010 በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአገሪቷ ምእራባዊ አጋማሽ የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው ብሔራዊ የሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። የሚጠበቀው የዝናብ ስርጭት በስፋት እየተከናወኑ ላሉ የግብርና ልማት ሥራዎች መልካም እድል እንደሆነም ተገልጿል። ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በተጠቀሱት ቀናት ምስራቅና ምእራብ ወለጋ፣ ጂማ ፣ ኢሉ አባቦራና አብዛኛዎቹ የሸዋ ዞኖች፣ ምእራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ አርሲና ባሌ ዞኖች እንደዚሁም አዲስ አበባ ከመደበኛው ጋር የተቀራረበና አልፎ አልፎም በጥቂት ቦታዎቻቸው ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ኤጀንሲው አመላክቷል። ከዚህም ሌላ የባሕር ዳር ዙሪያን ጨምሮ የምስራቅና ምእራብ ጎጃም አንደዚሁም የሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ተመሳሳይ መጠን ያለው የዝናብ ስርጭት ይኖራቸዋል ተብሏል። በተመሳሳይ ከትግራይ ክልል የምዕራብና መካከለኛው ዞኖች፣ የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አብዛኛው ዞኖች ከመደበኛው ጋር የተቀራረበና አልፎ አልፎም በጥቂት ቦታዎቻቸው ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ኤጀንሲው ጠቅሷል። በአንጻሩ በኦሮሚያ ቦረናና ጉጂ ዞኖች፣ በሶማሌ ክልል የጅግጅጋ እና የሲቲ ዞኖች በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ አነስተኛ ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመልክቷል። ቀሪው የሀገሪቷ ዞኖች ደረቅ ሆነው እንደሚሰነብቱም ትንበያው ያሳያል። ከመደበኛው ጋር ተቀራራቢ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች የአፈር እርጥበትን ለመጠበቅና ቀድመው የተዘሩ ሰብሎችና ቋሚ ተክሎች እንደዚሁም የጓሮ አትክልቶች የውኃ ፍላጎታቸውን ከማሟላት አንጻር ከፍተኛ አቅም እንዳለው ኤጀንሲው ጠቅሷል። የአየር ሁኔታው በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚጠበቀው እርጥበት የውኃ ፍላጎትን ለማሟላት፣ የግጦሽ ሳርና የሳር ልምላሜን እንዲሁም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምንጮችን ልምላሜ ለማጎልበት ያግዛል። በሌላ በኩል በዝናቡ ምክንያት ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ከአፈር መሸርሸርም ሆነ ከመሬት መንሸራተት ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኤጀንሲው አስጠንቅቋል።