ድርጅቱ ለሰላምና ልማት ሊሰራ ይገባል ተባለ

86
ሚያዝያ 14/2011 የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ ጋህነን/ በአገሪቱ የተፈጠረውን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በመጠቀም ለህዝቡ ሰላምና ልማት ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ። መቀመጫውን ኤርትራ በማድረግ የትጥቅ ትግል ላይ የነበረው የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ ጋህነን/ ለሰላማዊ ትግል ትናንት ወደ ክልሉ ገብቷል። ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለድርጅቱ አመራሮችና አባላት ባስተላለፉት የአቀባበል መርሐ ግብር ላይ እንዳሳሰቡት የክልሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ ለክልሉ ህዝብ ሰላምና ልማት ጥቅም መሥራት ይጠበቅባቸዋል። መንግሥት የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት በውጭ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ በመግባት ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምቹ  ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል። በመሆኑም ጋህነንም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተፈጠረውን ምቹ  ሁኔታ መጠቀም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የክልሉ መንግሥትና መሪ ድርጅት የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ጋህአዴን) ልዩነቶችን በማጥበብ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራም ተናግረዋል። መቀመጫውን በኤርትራ በማድረግ የትጥቅ ትግል ሲካሄድ የነበረው ጋህነን ወደ ክልሉ በመግባት ሰላማዊ ትግሉን እንዲቀጥል የተደረገለትን ጥሪ ተቀብሎ በመምጣቱ  ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ ጋህነን/ መሪ አቶ ኡኬሎ ኡኪዲ በዚሁ ጊዜ እንደሉት ጋህነን ቀደም ሲል ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ የትጥቅ ትግልን አማራጭ በማድረግ ሲታገል ቆይቷል ብለዋል። ይሁን እንጂ በቅርቡ በአገሪቱ የተካሄደው ለውጥ በውጭ ያሉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገራቸው በመግባት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርጉ በተላለፈው ጥሪ መሠረት የትጥቅ ትግሉን በመተው ወደ አገራቸው መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ጋህነን ቀደም ሲልም የዜጎች ሰብዓዊ የመብት ጥሰትና የልማት ተጠቃሚ ያለመሆን አሳስቦት ወደ ትግል መግባቱን ያስታወሱት የድርጀቱ መሪ፣ ለህዝቦች ሰላምና ልማት ከክልሉ መንግሥትና መሪ ድርጅት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። የክልሉ መንግሥትና ህዝብ ላደረገላቸው መልካም አቀባበልም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም