በተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ

115
አምቦ  ሚያዝያ14/2011  በምዕራብ ሸዋ ዞን ጌዶ ከተማ  ትላንት በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ። በአደጋው  15 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። የጨሊያ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ዱጋሳ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለፁት የእህል ማዳበሪያ ጭኖ ከአዲስ አበባ ወደ ነቀምቴ ከተማ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 –64641 ኢት የሆነ ከባድ ተሽከርካሪ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ጌዶ ከተማ ላይ እግረኞችን በመግጨቱ  አደጋው ደርሷል ። "አሽከርካሪው  የእጅ ፍሬን ሳይስብ በመውረዱ ተሸከርካሪው የተደረገለትን ታኮ በመዝለል በመንገድ ይጓዙ የነበሩ 19 ሰዎችን በመግጨት አደጋ አድርሷል" ብለዋል ኢኒስፔክተር ዱጋሳ ። ከተገጪዎች መካከል የአራቱ ህይወት ወድያው አልፏል። በስምንት ሰዎች ላይ ከባድ፤ በሌሎች ሰባት ሰዎች ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የገለፁት ኢኒስፔክተሩ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በጌዶ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል ። እንደ ኢኒስፔክተሩ ገለጻ አሽከርካሪው ለጊዜው ያመለጠ ሲሆን በፖሊስ በኩል ክትትል እየተደረገበት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም