በሰሜን ወሎ ዞን የ376 ታዳጊ ሕፃናት ጋብቻ እንዲሰረዝ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ወሎ ዞን የ376 ታዳጊ ሕፃናት ጋብቻ እንዲሰረዝ ተደረገ
ሚያዝያ 14/2011 በሰሜን ወሎ ዞን ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት በተደረገ ጥረት ሊዳሩ የነበሩ 376 ታዳጊ ሕፃናት ጋብቻቸው እንዲሰረዝ መድረጉን የዞኑ ፍትህ መምሪያ ገለጸ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ አምባው መላኬ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የታዳጊ ህጻናቱ ጋብቻ ሊሰረዝ የቻለው ፍትህ መምሪያው በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ ነው።
በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ለጋብቻ ደርሰዋል የተባሉ 2 ሺህ 273 ታደጊ ህጻናት በጤና ተቋማት ቀርበው የዕድሜ ምርመራ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ምርመራውን ካደረጉት መካከልም 376 ዕድሜያቸው ባለመድረሱ ጋብቻው እንዲሰረዝ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
አቶ አምባው እንዳሉት ህጻናት ያለዕድሜያቸው ሊዳሩ ሲሉ ከተከላካይ ግብረ ኃይል፣ ከቀበሌ አመራሮችና ከሌሎች አካላት ለመምሪያው ጥቆማ ይደርሳል።
የሚደርሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግም የህጻናቱ ፎቶ ግራፍና ማስረጃ ታሽጎ ለምርመራ ወደጤና ተቋማት እንደሚላክ ጠቁመዋል፡፡
"በምርመራ ውጤቱ መሰረት ዕድሜያቸው 18 እና ከእዚያ በላይ የሆናቸው ጋብቻ እንዲፈጽሙ ፣ ዕድሜያቸው ያልሞላም መረጃው ለቀበሌ አመራሩና ለተከላካይ ግብረ ኃይሉ ተልኮ ጋብቻው እንዲቋረጥ ይደረጋል" ብለዋል፡፡
ያለዕድሜ ጋብቻ አማካይነት ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስም ዘንድሮ በደጋማ ወረዳዎች ከ3 ሺህ 700 ለሚበልጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
ያለዕድሜ ጋብቻን ለመከላከል ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ ሁለት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአምስት ወረዳዎች በሚገኙ 50 ትምህርት ቤቶች እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
"አንፕካን" የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አስተባባሪ አቶ ጋሻው አለባቸው በበኩላቸው ያለዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ በህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዶችን ለመቀነስ ከሕብረተሰቡ ጋር ተባብረው እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ያለዕድሜ ጋብቻ ታዳጊ ሕጻናት ትምህርት እንዲያቋርጡ ከማድረግ ባለፈ አካላቸው ሳይጠነክር ስለሚወልዱ ለፌስቱላ ጉዳት ተጋልጠው ለከፋ የስነ ልቦና ጫና እንደሚዳረጉ አስረድተዋል፡፡
በመቄት ወረዳ "የአግሪት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት" መምህርና የሥነ ተዋልዶ ክበብ አስተባባሪ ወይዘሮ ለምለም አብርሃ በሰጡት አስተያየት የክበቡ አባላት ያለዕድሜ ጋብቻን በመጠቆም እንዲቋረጥ በማድረግ የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል።
" ዘንድሮ ለትምህርት ቤቱ የደረሰውን 10 ያለዕድሜ ጋብቻ ጥቆማ ከወላጆች ጋር በመነጋገር የሰባት ታዳጊ ህጻናት ተማሪዎች ጋብቻ ለማቋረጥ መቻሉን በማሳያነት " ጠቅሰዋል፡፡
በእዚሁ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አብርሃም ፈንታየ በበኩሉ ባለፈው ጥር ወር ወላጆቹ 12 ዓመት የሞላት እህቱን ሊድሩ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ለትምህርት ቤቱ ጥቆማ ሰጥቶ ጋብቻው እንዲቋረጥ ማድረጉን ተናግሯል፡፡