የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ወደ አገሩ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ወደ አገሩ ገባ
ጋምቤላ ሚያዝያ 13/2010 መቀመጫውን ኤርትራ በማድረግ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የቆየው የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ዛሬ ወደ ጋምቤላ ክልል ገብቷል።
ለድርጅቱ አመራሮችና አባላት በጋምቤላ ኤር ፖርት የክልሉ ከፍተኛ አመራርና ሕዝብ ለድርጅቱ አቀባበል አድርገውለታል።
የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ኦኬሎ ዑኩዲ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ለሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ባቀረበው ጥሪ መሠረት ንቅናቄው ወደ አገሩ መመለሱን ገልጸዋል።
በዚህም ከክልል መንግሥትና መሪው ድርጅት ጋር በመሆን ለሕዝቡ ተጠቃሚነት ለመሥራት መወሰናቸውን አስታውቀዋል።
የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዑሞድ ዑጁሉ ድርጅቱ የመንግሥትን ጥሪ ተቀብሎ በመምጣቱ አመስግነዋል።
ከድርጅቱም ሆነ ከሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶች ጋር ልዩነቶች ቢኖሩም፤የክልሉ መንግሥትና መሪው ድርጅት ለክልሉ ሕዝቦች ጥቅም በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በክልሉ የሚደረገው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ድጋፍ እንደሚያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡