የአማራና ኦሮሞ ግንኙነትን በማጠናከር የተጀመረውን የፖለቲካ ምዕራፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ይገባል- አቶ አዲሱ አረጋ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራና ኦሮሞ ግንኙነትን በማጠናከር የተጀመረውን የፖለቲካ ምዕራፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ይገባል- አቶ አዲሱ አረጋ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2011 የአማራና ኦሮሞን ህዝብ አብሮነት፣ አጋርነትና ወንድማማችነትን በማጠናከር በአገሪቷ የተጀመረውን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማእከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ።
የአማራና ኦሮሞ ወንድማማች ህዝቦችን ግንኙነት የሚያጠናክር መድረክ በአምቦ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በህዝብ ለህዝብ መድረኩ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማእከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እንደገለጹት የአማራና ኦሮሞ ህዝብ አብሮነት፣ አጋርነትና ወንድማማችነትን በማጠናከር የተጀመረውን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ወደ ተሻላ ደረጃ ማድረስ ይገባል።
የአማራና ኦሮሞ ህዝብ በባህል፣ በአስተዳደር ወሰን፣ በቋንቋ፣ በስነ ልቦና፣ በታሪክና በማህበራዊ መስተጋብር ካላቸው የቆየ ትስስር በላይ የደም ትስስር ያላቸው ህዝቦችና ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ መስዋትነት የከፈሉ ናቸው ብለዋል።
ይህም በጣሊያን ወረራ ወቅት ጣሊያንን በመጀመሪያውና ዳግም በመጣ ጊዜም ህይወታቸውን በመገበርና በቅርቡ ደግሞ ለፍትህና ለዴሞክራሲ ወሳኝ ትግል ያደረጉ ህዝቦች እንደሆኑ በማስታወስ።
ይሁንና ፖለቲከኞችና ሊሂቃን የተሳሳቱ ትርክቶችን በማራመድ ሁለቱን ህዝቦች ለመከፋፈል ከፍተኛ ትግል ሲያካሂዱና እያካሄዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች የማይስማሙ ህዝቦች ተደርገው ለብዙ ጊዜ ሲነገሩ ከነበሩ የተሳሳቱ ትርክቶች ማዕከል ነበሩ ሲሉም ተናግረዋል።
በተለይም አማራና ኦሮሞ የማይታረቁና አብረው መኖር የማይችሉ ለማስመሰል ገንዘብ ተበጅቶ ብዙ ስራ ሲሰራ እንደነበረ ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ አንዱ በተስፋዬ ገብረአብ የተፃፈው የቡርቃ ዝምታ መፅሃፍ ተጠቃሽ ነው ሲሉ አስታውሰዋል።
ሁለቱ ህዝቦች በተለይም ቄሮና ፋኖ ባለፉት ሶስት ዓመታት የሃሳብ ነጻነት እንዲሰፍን ፣ ፍትሃዊነትና የሃብት ክፍፍል እንዲኖር፣ የተደራጀ ሌብነትንና የአንድ ቡድን የበላይነት እንዲቀር በጋራ ባደረጉት ትግል በአገሪቷ ለውጥ እየተመዘገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ የሰቆቃ ምዕራፍ እንዲዘጋ ፣ የዜጎችና የአገር ክብር እንዲመጣ፣ በሽብር የተፈረጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ወደ አገርቤት እንዲገቡ እንዲሁም የሪፎርም ስራ በሁሉም መስክ እንዲሰራ፣ የተደራጀ ዝርፊያ እንዲቆም የማድረግ ስራ ተሰርቷል።
በአሁኑ ወቅት ለውጡ በመልካም ሁኔታና በተገቢው መንገድ እየሄደ ቢሆንም ለውጡን ለመቀልበስ የሚሰሩ ቡድኖችና ጽንፈኛ ብሔርተኝነት የለውጡ ተግዳሮት መሆናቸውንም አቶ አዲሱ አልሸሸጉም ።
ስለሆነም በቀጣይ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይም የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች በጋራ በመሆን ጽንፈኛ ብሔርተኝነትን መታገል፣ በአንዳንድ ሊሂቃንና በፖለቲከኞች የሚሰራጩትን የሐሰት ትርክቶችን እንደ አገር ወዳድ የማረም ተግባራት ማከናወን ተገቢ ነውም ብለዋል።
ለዚህም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር፣ የባህልና ኪነጥበብ ትስስርን ማጎልበት፣ የሰላምና የአብሮነት እሴቶች እንዲጠናከሩ ማድረግ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች የመመለስ ስራ መስራትና ባለፉት ጊዜያት የተበላሹ ስራዎችን የማስተካከል ስራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል።