የመከባበርና የመቻቻል እሴቶችን ለማጎልበት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የመከባበርና የመቻቻል እሴቶችን ለማጎልበት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ
ሐረር ሚያዝያ 13/2011 የክልሉን ሰላም በማጠናከርና የመከባበርና የመቻቻል እሴቶችን በማጎልበት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሐረሪ ክልል የሃይማኖት አባቶች አረጋገጡ።
የሐረሪ ክልል የሰላም ኮንፍረንስ ዛሬ ተካሂዷል።
የሃይማኖት አባቶቹ በኮንፍረንሱ ላይ እንደተናገሩት በሃይማኖት ሽፋን የሚከናወን ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ በመከላከል ፣ የነዋሪዎችን የመከባበር እሴት በማጎልበት እና ለሰላም በአንድነት እንዲቆም በማድረግ ሚናቸውን ይወጣሉ፡፡
ከሃይማኖት አባቶቹ ሼህ ፈይሰል አህመድ የእስልምና አስተምህሮት አንድነትን ፣ መደጋገፍን ፣ መዋደድንና ይቅር ባይነትን አንደሚያስተምር ገልጸው፣ ስለሆነም በጎሳ፣ በቀለምና በሃይማኖት ሳንከፋፈል ሰላምና አንድነታችንን ማጠናከር ይገባናል ብለዋል፡፡
ክልሉ የተለያዩ ብሔረሰቦችና እምነት ተከታዮች በአብሮነት የኖሩበት እሴት እንዳለው፤ እሴቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ጥረት አደርጋለሁ ብለዋል።
የክልሉ ሰላም እንዲጠናከር የእምነቱ ተከታዮችን በማስተማር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የወከሉት ሊቀ መልዓክ ፍስሃጽዮን አደመ ናቸው፡፡
የክልሉ ፀጥታ እየተሻሻለ መምጣቱንና የሕዝብ ጥያቄዎች እየተመለሱ መሆናቸው እንዲጠናከሩ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያንን የወከሉት አቶ ገናናው ተክለወልድ ለክልሉ ሰላምና ልማት ድርሻቸወን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የረመዳን ፆም የሚገባበት ወቅት መቃረቡን በማስታወስ የተናገሩት የሐረሪ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ መሀመድ አሚን የተጣላውን በማስታረቅ፣ የተራበውን በማብላትበ ሰላምና በአንድነት አስተምህሮታችንን እናጠናክራለን ብለዋል፡፡
'የክርስትናም ሆነ የእስልምና እምነት የሰላም ሃይማኖቶች ናቸው'' ያሉት ሌላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባት አባ መላከ ኪዳነማርም ሲሆኑ፤በሀይማኖቶች ሽፋንና ስም የሚደረጉትን ትንኮሳዎችና ለግጭት የሚዳርጉ እንቅስቃሴዎችን በመከላከል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተደድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደገለፁት በክልሉ ከስድስት ወራት በፊት የሕግ ጥሰቶች ሲፈፀሙ ከነበሩበት አሁን እየተቀየረ መምጣቱን አመልክተው፣ ሰላምና አንድነት እየጠነከረ መምጣቱን አስረድተዋል፤ ለዚሀም ኅብረተሰቡ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ከሕግ የበላይነትን በማረጋገጥና ሃይማኖትን ተገን የሚያደረጉ ትንኮሳዎች የክልሉ መንግሥት እንደማይታገስ አመላክተዋል፡፡
ክልሉ ቀደም ሲል የተፈጠሩ ችግሮችን እያረመ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሰላምን ዘላቂ በማድረግ ዜጎች ካለ ስጋት ሰርተው የሚኖሩበት አገርና ክልል ለመፍጠር እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
ኮንፈረንሱ የተዘጋጀው በክልሉ ፍትህና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ነበር።