አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ማበረታታት ወጣቶች አርአያነታቸውን እንዲከተሉ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ማበረታታት ወጣቶች አርአያነታቸውን እንዲከተሉ ያስችላል
ግንቦት 27/2010 አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ማበረታታት ወደሙያው የገቡ ወጣቶች አርአያነታቸውን እንዲከተሉ ከማድረግ ባለፈ ለጥበቡ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጡ በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተጠቆመ። "ባህላዊ እሴቶቻችን ለሰላማችንና አብሮነታችን" በሚል መሪ ቃል ለአምስት ተከታታይ ቀናት በጉጂ ዞን ሲካሄድ የቆየው ስድስተኛው ዙር የኦሮሚያ ክልል የባህልና ዝክረ ኪነጥበብ መድረክ ትናንት ተጠናቋል። በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሎሚ በዶ እንዳሉት በኪነ-ጥበብ ውስጥ ለትውልድ የሚተላለፍ አሻራቸውን የሚያኖሩ አንጋፋ የኪነጥበብ ሰዎች ሊዘከሩ ይገባል ፡፡ አንጋፋዎቹ እንዲበረታቱ መደረጉ ለተተኪ ወጣት የዘርፉ ባለሙያዎች ተስፋ ከመሆን ባለፈ አርአያነታቸውን እንዲከተሉና ለጥበቡ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በአንድነት የመኖር ባህል አለው ያሉት" ኃላፊዋ ይህን አኩሪ ባህል በማዳበር ማስቀጠል አንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ በእለቱ በኦሮምኛ ቋንቋ ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው አርቲስት ፀጋዬ ደንደና እና የኦሮምኛ ቴአትርና ድራማ ደራሲና ጋዜጠኛ ዳባ ወዬሳ ላኪነ ጥበቡ እድገት ለበረከቱት አስተዋጽኦ ተዘክረዋል። እያንዳንዳቸው ብር 50 ሺህ የተበረከተላቸው ሲሆን የዕውቅናና የምስጋና ምስክር ወረቀትም ተሰጥቷቸዋል፡፡ አርቲስት ፀጋዬ ደንደና በመርሀ-ግብሩ ላይ ተገኝቶ የተበረከተለትን የማበረታቻ ሽልማትና የምስክር ወረቀት ሲቀበል ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው ደራሲና ጋዜጠኛ ዳባ ወዬሳ በሥራ አጋሩ አቶ ተስፋዬ መኮንን አማካኝነት ተቀብሏል ፡፡ አርቲስት ፀጋዬ ደንደና ከ100 በላይ ሙዚቃዎች እንዳሉታና ዘጠኝ አልበሞችን ማዘጋጀቱ ተነግሯል፡፡ አርቲስቱ የግጥምና ዜማ ደራሲ ከመሆን ባለፈ ግጥሞቹም በርካታ ርዕሶችን የሚዳስሱና ተስፋ ያዘሉ መሆናቸው ነው የተነገረው። ደራሲና ጋዜጠኛ ዳባ ወዬሳ ደግሞ ቴአትርና ድራማ በመድረስና በማዘጋጀት እንዲሁም ፊልም በማዘጋጀት እንደሚታወቅ ተገልጿል፡፡ በአሁን ወቅትም በአሜሪካ ድምጽ የሬዲዮ ዝግጀት ክፍል ውስጥ እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል ፡፡ አርቲስት ፀጋዬ ደንደና በበኩሉ ሥራዎቹ ዕውቅና አግኝተው ይህን ክብር በማግኘቱ ደስታ እንደተሰማው ገልጾ ሽልማቱም ይበልጥ ለመስራት እንዳነሳሳው ተናግሯል፡፡ " በእንዲህ አይነት የዝክረ ኪነ-ጥበብ መድረክ አንጋፋዎች መታወሳቸው ሌሎች አርቲስቶች በሙያው ውስጥ እንዲቆዩ፣ ልምድ እንዲቀስሙና እንዲበረታቱ ያደርጋል " ብሏል፡፡ ለዘርፉ እድገት መስዋዕትነት የከፈሉ በርካታ ባለሙያዎች መኖራቸውን ያስታወሰው አርቲስት ፀጋዬ እነዚህ ባለሙያዎች በተመሳሳይ መድረክ ሊታወሱ እንደሚገባና ስራዎቻቸውም ተሰብስበው በአግባቡ ሊጠበቁ ይገባል ነው ያለው፡፡ የምዕራብ አርሲ ዞን የባህል ኪነት ቡድን ድምጻዊ የሆነው ወጣት ቂልጡ ጫቂሶ በበኩሉ "አርቲስት ፀጋዬ በዘርፉ አርአያ የሚሆን ስብዕና ያለው ድምጻዊ እንደሆነ ገልፆ "ለባለሙያዎቹ የተበረከተው ዕውቅናና ሽልማት የእነሱን ፈለግ ለመከተል አነሳስቶኛል" ብሏል ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል ከኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ መድረክ ላይ ከ13 ዞኖችና ስድስት ከተማ አስተዳደሮች በመጡ የባህል ልዑካን ቡድኖች መካከል የኪነ ጥበብ ትርኢትና ውድድር ተካሂዷል። ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን ያገኙት የነቀምት ከተማ፣ የቢሾፍቱ ከተማና የጉጂ ዞን ቡድኖች የተዘጋጀላቸውን ዋንጫ ና የ20 ሺህ፣ የ15 ሺህ እና የ10 ሺህ ብር ሽልማት ተቀብለዋል፡፡