ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ ለችግር የሚዳረጉ ዜጎችን ለመርዳት የሚያስችል ስምምነት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር አደረገ

ሚያዝያ 12/2011 የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን በጋራ ለመርዳት የሚያስችል ስምምነት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር አደረገ።

በደረሰው ስምምነት መሰረት አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በጋራ መደገፍ ያስችላል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ጌታነህ አብዲሳ በዚሁ ጌዜ እንዳሉት የሃይማኖት ተቋማት "ለወገን ደራሽ ወገን ነው" የሚለውን መርህ አንግበው ዜጎች ከችግር እንዲወጡ በመስራታቸው አመስግነዋል።

በልመና ላይ ለተሰማሩ ዜጎች ዘላቂ መፍትሄ በማበጀት "ልመናን አማራጭ" እንዳያደርጉ በማስተማርና የአቅማቸውን ሰርተው እንዲኖሩ የሃይማኖት አባቶች በምክራቸው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸክ መሃመድ አሚን ጀማል በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በበጎ ተግባር መተባበር መልካም መሆኑንን በመጥፎ ምግባር መተባበር ደግሞ የተወገዘ ወይም ሃራም መሆኑን ሃይማኖቱ ያስተምራል።

በመሆኑም የእምነቱ ተከታዮች በእንዲህ አይነት በጎ ምግባር ተባባሪ በመሆን ሃይማኖታዊ ግደታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህ ዘመን የኢትዮጵያውያን ባህላዊ እሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩ "ዘመናዊነት" በሚል ሰበብ ግለኝነት እየተጠናወተ በመምጣቱ በሁሉም ዘንድ ሊታረም ይገባልም ነው ያሉት።

መንግስትም በተለይ ወጣቶች አገራዊ ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ በትምህርት ቤትም ይሁን በሌሎች ማህበራዊ ተቋማት ማስተማር ይኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት አብያተ ክርስትያን ህብረት ፕሬዘዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው በስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ውስጥወጣቶች መብታቸውን ብቻ ሳይሆን ግዴታቸውንም እንዲያውቁ ማስተማር  ይገባል ብለዋል።

"በአገሪቷ ያሉ ባህላዊ እሴቶች እየደበዘዙ በመምጣታቸው በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ያለው አንድነት እየላላ መጥቷልም" ነው ያሉት።

በሁሉም እምነት መልካም ስራን እንደሚያበረታታ በመግለጽ የተለያዩ እምነት ተከታዮች ለበጎ ስራ እንዲሰለፉም ጥሪ አቅርበዋል።

በማህበረሰቡ ውስጥ ልዩነት መኖሩን አምኖ በልዩነት ውስጥ ባለው አንድነት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቶበታል።

እስካሁን ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለመርዳት አራት የ``ሃይማኖት ተቋማት ከሚኒስቴሩ ጋር ስምምነት የፈረሙ ሲሆን ቀሪዎቹም በቀጣይ ይህንኑ መልካም እሳቤ እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም