የንግድና ኢንዳስትሪ ሚኒስቴር የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የንግድና ኢንዳስትሪ ሚኒስቴር የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ እያደረገ ነው
ሚያዝያ 12/2011 የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአሠራር ሥርዓቱን ቀላልና ቀልጣፋ ለማድረግ መመሪያዎችንና አዋጆች በመከለስ በቴክኖሎጂ መጠቀም መጀመሩን ገለጸ፡፡
ባለፈው አንድ አመት የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አስደግፎ እየሰጠ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዮሃንስ ድንቅአየው ገልፀዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጡ 1ሺህ 134 ጣቢያዎች ውስጥ ቀደም ሲል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም በማስደገፍ አገልግሎቱን የሚሰጡ ጣቢያዎችን ከ892 ወደ 1049 ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚሰጠውን የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አገልግሎት በቀጥታ ለመከታተልና በአገልግሎት ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቀነስ የሲሲቲቪ ካሜራ እና የወረፋ ማስያዣ ማሽን ስራ ላይ መዋሉንም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ መደቦችን በመከለስ “የኢትዮጵያ ንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ መደብ መመሪያ ቁጥር 17/2011” ጸድቆ ወደ ሥራ መገባቱን ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል የንግድ አሠራር ሥርዓቱን ቀላልና ሳቢ ለማድረግ የአስገዳጅ ደረጃዎች ማስፈፀሚያ ረቂቅ አዋጅ እና የሕጋዊ ስነ-ልክ ረቂቅ አዋጅ ተጠናቆ ለካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ጽ/ቤት መላኩ ተገልጿል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን አዋጅ ቁጥር 551/1999 ማሻሻያ ተጠናቆ ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተልኳል ብለዋል።
ወደ ውጭ የሚላኩ የቡና፣ ሰሊጥና አኩሪ አተር ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ከአምራቾች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
በአገር ውስጥ የምርት አቅርቦት እጥረትና ያለውን በተገቢ ሁኔታ ያለማዳረስ ችግርን ለመፍታት ጥናት ተካሂዶ የአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪው እንዲገቡና በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉት ባለሃብቶችም ያለባቸውን ችግሮች በመፍታት በተሻለ አቅም እንዲሰሩ የማበረታታት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ወደ ተቋሙ በተደጋጋሚ የተለያዩ አገልግሎት ፈልገው እንደሚመላለሱ የጠቆሙት ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ተገልጋይ፤ የድርጅታቸውን አድራሻ ለመቀየር የካፒታል መጠንን በትክክል ለማስመዝገብ መጥተው የፈለጉትን ያህል ባይሆንም ምላሽ ማግኘታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
ከአንድ ዓመት ለውጥ ወዲህ አገልግሎት አሰጣጡ ከበፊቱ የተወሰኑ መሻሻሎች ቢኖሩም በነበሩበት የቀጠሉ እንዳሉ ግን አልሸሸጉም።
በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ስህተት ተፈጥሮ ማስተካከያ ሲጠየቅ የማመላለስ ሁኔታ ይስተዋላል ያሉት አስተያየት ሰጪው በቀላሉ መጨረስ የሚችሉትን ጉዳይ ለማስፈፀም ከሳምንት በላይ እንደወሰደባቸው ይናገራሉ፡፡
የንግድ ፈቃዳቸውን ለማደስ የመጡት ሌላው ተገልጋይ አቶ ሩፋኤል ንጉሴ እንደሚሉት አገልግሎት አሰጣጣቸው ከበፊቱ የተሻለ፣ቀልጣፋና ምቹ ነው።
በዚህ ተቋም መገልገል ከጀመሩ 6 አመታት እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ ሩፋኤል፤ አሁን ላይ አገልግሎት አሰጣጡ እንደበፊቱ ግፍያና መጉላላት እንደሌለው ጠቁመው “ከለውጡ ጋር ተያይዞ ይመስለኛል በተለይም በዚህ አመት የተቀላጠፈ አገልግሎት እያገኘን ነው” ብለዋል፡፡
አቶ አብዲ ኑረዲን የምድብ “ሀ” ተጠቃሚነት የምስክር ወረቀት የካርድ ክፍያ ለመፈጸም ፍላሚንጎ አካባቢ ከሚገኘው ኢንዳስትሪ ሚኒስቴር ሂልተን ወደ ሚገኘው ንግድ ሚኒስቴር መምጣት ግድ እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡
ስራቸው አንድ ሆኖ ቢሮው የተለያየ ቦታ መሆኑ በአገልግሎት ሰጪዎቹ አለመናበብ ፈጥሮ አንደኛው ይሆናል ያለው አንደኛው አይሆንም በሚል በወረቀት ስራ ብቻ በመመላለስ ጊዜያቸውን እያጠፉ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ስለ ጉዳዩ እንዳብራሩት ሁለቱን ሚኒስቴር መስሪያቤቶች በማዋሃድ መዋቅሩ መደራጀቱንና ተቋማቱ በተለያየ ቦታ በመሆናቸው የተፈጠረውን የአገልግሎት ችግር ለመፍታት የሁለቱን ተቋማት ሰራተኞች መያዝ የሚችል ህንፃ ለመከራየት በጨረታ ሂደት ላይ ናቸው።