ቀጥታ፡

በኬኒያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ለዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ገቢ ለማሰባሰብ ይወያያሉ

ሚያዝያ 12/2011 በኬኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም መቀመጫቸውን ኬንያ ላደረጉ ዓለም ዓቀፍና የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በኬኒያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በአገራችን ጉዳይ ያገባናል በሚል እየተንቀሳቀሱ ነው።

ኢትዮጵያ ቀጣናውን ሰላም ለማድረግ ከጎረቤቶቿ ጋር በመተባበር እንደምትንቀሳቀስ ገልጸው ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ ከኬኒያ ጋር በቅርበት ትሰራለች ብለዋል።

ኢኮኖሚያዊ ትብብሩን ለማጠናከር የተጀመረው ፕሮጀክት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ አፈጻጸም እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ለጎረቤት አገራት ጉዳይ ትኩረት ይሰጣል ያሉት አምባሳደር መለስ ‘’ከኬንያ ጋር ለአሁንና ለመጪው ጊዜ የጠበቀ ወዳጅነት ይሰራል’’ ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃኑ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በጠንካራ ለውጥ ላይ መሆኗን ያመለከቱት አምባሳደር መለስ ለውጡ ግለቱን ጠብቆ እየሄደ ስለመሆኑም አመልክተዋል።

የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ እንቅስቃሴን ለማጠናከር በኬንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዲያስፖራው ለአገሩ ልማት የበኩሉን እንዲወጣ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በኬኒያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የድርሻቸውን ለመወጣት እየሰሩ ይገኛሉ ሲሉም ተናግረዋል።

ኤምባሲውም ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ላይ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በኬኒያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ገቢ ለማሰባሰብ የሚያስችላቸውን ውይይት ከማህበረሰቡ ጋር ለማካሄድ ዝግጅት አጠናቀዋል።

ኤምባሲው ለዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ኮሚቴ እንቅስቃሴ የድርሻውን አስተዋጽኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

በኬኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም በውጪ የሚኖሩ ዜጎች የአገራቸው እንደራሴ በመሆናቸው በገጽታ ግንባታ፣ ልማት እና ሌሎችም መስኮች አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም