ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በርካታ ሥራዎች ይጠበቁባታል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በርካታ ሥራዎች ይጠበቁባታል
አዲስ አበባ ሚያዝያ 11/2011 ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት በርካታ ሥራዎች መሠራት እንደሚጠበቅባት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።
አምባሳደር ፍጹም በአሜሪካ በዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ አስተባባሪነት ዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ወይም ሪፖርተር ዊዝ አውት ቦርደር እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2019 ያወጣውን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ደረጃ ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ተሳትፈዋል።
የድንበር የለሽ የጋዜጠኞችቡድን ሪፖርት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ከዓለም የመገኛኛ ብዙኃን ነጻነት ሠንጠረዥ 40 ደረጃን አሻሽላለች።
አምባሳደር ፍጹም እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ አመራር ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ በርካታ ለውጦች መጥተዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም መገናኛ ብዙኃንና በሠብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች የምትነቀፍበትን የሠብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ለውጥ አስመዝግባለች።
ይህንንም በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ማድረጋቸውንና አጠቃላይ ለውጡ መሠረታዊ የህግ ሥርዓትን ተከትሎ መተግበሩን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በተለይም ልዩነቶችን በማስተናገድና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ላይ ክፍተት መኖሩን ተናግረው ለዚህም የአቅም ግንባታ ትፈልጋለች ብለዋል።
በተለይም የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት ዴሞክራሲን ለማስረጽ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ በዚህም የአቅም ግንባታ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመገናኛ ብዙኃንን በኃላፊነትና ሚዛናዊነትን ባረጋገጠ መልኩ መጠቀም እንደሚገባም አስረድተዋል።
ሕዝቡም እንዴት የመገናኛ ብዙኃንን መጠቀም እንዳለበት አቅሙ ሊጎለብት ይገባል ነው ያሉት።
ያም ሆኖ በተረጋጋ ዴሞክራሲ ውስጥ እንዳለው ማኅበረሰብ የዴሞክራሲ ሥርዓት ገቢራዊ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ይጠይቃሉ ብለዋል።
ትምህርትና የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት አስፈላጊ መሆኑን አምባሳደሩ አስምረውበታል።
ፌስ ቡክ ምንም እንኳን መረጃን ለመለዋወጥ ሠፊ ምህዳር ቢፈጥርም አላስፈላጊ መረጃዎችን በመልቀቅ የራሱ ችግር እንዳለው ተናግረዋል።