ቀጥታ፡

በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ የባለድርሻ አካለት ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል --- ወይዘሮ የአለም ፀጋይ


አዳማ ሚያዝያ 11/2011 በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ያሉትን ማነቆዎች ለይቶ  ለማስወገድ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ርብርብ እንደሚያስፈልግ የሴቶች ፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር  ወይዘሮ የአለም ፀጋይ ገለጹ።

በሥራ እድል ፈጠራ አተገባበርና አፈፃፀም ዙሪያ ያሉትን ክፍተቶች ለመለየትና የጋራ የመፍትሄ ለማስቀመጥ የተዘጋጀ  የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

ሚኒስትሯ በመድረኩ እንዳሉት ወጣቱ ኃይል በልማቱ ውስጥ ንቁ ተሳትፍ እንዲኖረው ተገቢውን ድጋፍና እገዛ በማድረግ እውቀቱንና ጉልበቱን አቀናጅቶ ወደ ሥራ ማስገባት ይገባል።

ይህም ህዝቡንም ሆነ  ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣት ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል።

ሥራ አጥነት የወጣቶችን ስነልቦና በመጉዳት ሀገሪቱን ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች የሚደርግ በመሆኑ  በአሰራር የሚስተዋሉ ክፍተቶች በተለይም በሥራ ፈጠራ፣ በብድር አገልግሎትና የቁጠባ ባህል በማዳበር ላይ ተባብሮ መስራት ይጠይቃል።

ከአመለካከት፣ ከመፈፀምና ማስፈፀም ጋር ቁርኝት ያላቸው የአቅም ማነስ ፣ ከግሉ ባለሃብትና የዘርፉ አደረጃጀቶች ጋር ያለው ትስስር ደካማነት፣የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር መጨመርና የፋይናንስ አቅርቦት ውስብስብነት አሁንም ቁልፍ ችግር መሆኑን ሚኒስትሯ ያመላከቷቸው ናቸው።

በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ያሉትን እነዚህን ማነቆዎችን ለማስወገድ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የመድረኩ ዓላማ የግሉ ባለሃብት እስከ ዛሬ በሥራ እድል ፈጠራ ውስጥ የነበረውን ሚና አጠናከሮ ለማስቀጠልና በቀጣይነት በከተሞች ድህነት ለማስወገድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲሆን ለማስቻል ጭምር እንደሆነ አብራርተዋል።

"የወጣቶች የቁጠባ ባህል ደካማ መሆን፣የሀገሪቱ የብድር አገልግሎት የህግ ማእቀፎች ውስብስብነት፣የአስተሳሰብና አመለካከት ማነቆዎችን ለማለፍ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር አለበት" ያሉት ደግሞ የከተሞች የሥራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጄንስ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ መንግስቱ ናቸው።

በኢንዱስትሪዎችና አምራቾች መካከል ጥራትን መሰረት ያደረገ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ፣የቴክኖሎጂ ሽግግር ማፈጠን፣የፈጠራ ውጤቶች ማበረታታትና ማስፋፋት፣የቴክንክና ሙያ ትምህርት ስልጠናን አቅም መገንባት ላይ በትኩረት ማስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን  እቅድ ዘመን መጨረሻ ከ8 ሚሊዮን 400ሺህ  በላይ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠርና ድህነትን ለመቀነስ ግብ መቀመጡን አስታውሰዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት ከ4 ሚሊዮን ለማይበልጡ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን የጠቆሙት አቶ በቀለ  "በቀጣዩ ዓመት ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑት ሥራ መስጠት መቻል አለብን" ብለዋል።

ለዚህም በአደረጃጀት፣አሰራር፣አቅርቦት፣ስልጠናና አቅም ግንባታ ዙሪያ የሚታዩ ማነቆዎችን ከወዲህ ለመፍታት የባለድርሻ አካላትና ባለሃብቶች ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

በመድረኩ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም