ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአፍሪካ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአፍሪካ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት ተባለ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 11/2011 ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአፍሪካ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ትኩረት መሥጠት እንዳለበት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ።
ሚኒስትሩ በአሜሪካ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በተካሄደው የፋይናንስ ፎረም ላይ ተሳትፈዋል።
በዚህ ጊዜ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ቅድሚያ የተሰጠው የሥራ ፈጠራ ነው፤ ይህም በከፍተኛ መጠን ለሚያድገው የሕዝብ ቁጥር ወሳኝ ነው።
ያም ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የሥራ አጥ ቁጥር በመኖሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጓል ብለዋል።
ይህም የሥራ ፈጠራ ጉዳይ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም እያደገ ለመጣው የወጣቶች ቁጥር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም ለውጭና ለአገር ውስጥ ባለኃብቶች ኢኮኖሚው ክፍት እንዲሆን በመንግሥት መወሰኑን ለአብነት የተወሰደውን እርምጃ ገልጸዋል።
ይህም በውድድር ላይ ለተመሰረተ የንግድ ሥርዓትና ዘላቂ የፋይናንስ ሥርዓት ለመፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በዚህም ላይ ቴክኖሎጂ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለእሱም ተመጣጣኝ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
ይህም የመሰረተ-ልማት ፋይናንስ ጉድለትን ለመሙላት ያግዛል ነው ያሉት።
በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ባለኃብቶች በአፍሪካ የሥራ ፈጠራ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ገልጸዋል።
እነዚህም ጉዳዮች በዓለም ምጣኔ ኃብት ላይ የራሳቸውን ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለይም ለታዳጊ አገራት በትንሽ ወለድ የሚቀርበው ብድር እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸው ለዚህም ትኩረት ይገባል ነው ያሉት።