ከጋምቤላ ወደ አዲስ አበባ ሲጓጓዝ የነበረ 780 ጥይትና አንድ ሽጉጥ ተያዘ

31

ሚያዝያ 10/2011 ከጋምቤላ ወደ አዲስ አበባ በተሽከርካሪ ሲጓጓዝ የነበረ አሽከርካሪ 780 ጥይቶችና አንድ ሽጉጥ ዛሬ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

በፌዴራል ፖሊስ የምዕራብ ዲቨዥን ሶስተኛ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ተረፈ  በለጠ ለኢዜአ እንደገለጹት አሽከርካሪው ከጥይቶቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉው በባሮ ወቆላ ኬላ በተደረገ ፍተሻ ነው።

ከጥይቶቹ  560 የክላሽንኮቭና 220 የብሬን መትረየስ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ጥይቶቹና ማካሮቭ ሽጉጥ የተያዙት ኮድ 2 የሠሌዳ ቁጥር አዲስ አበባ 69638 በሆነች ተሽከርካሪ እንደነበርም አመልክተዋል።

አሽከርካሪው በቁጥጥር ሥር ወሎ ጉዳዩ በመጣራት ላይ እንደሚገኝ ዋና ኢንስፔክተር ተረፈ አስታውቀዋል።

ፖሊስ ከግለሰቡ  ጋር  በግብረ አበርነት የሚጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ለመያዝ ክትትል እያደረገ ነው ብለዋል።

በክልሉ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እየተበራከተ መምጣቱን የጠቆሙት አዛዡ፣  ችግሩን ለመከለካል የኅብረተሰቡ ድጋፍና ትብብር እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

በክልሉ ባለፉት ስምንት ወራት የዛሬዎቹን ጨምሮ 4ሺህ 684 የክላሽንኮቭ ፣ 302 የብሬን፣ 79 የዲሽቃና 33 የሽጉጥ ጥይቶች ተይዘዋል።

በቅርቡም ከክልሉ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 11 ክላሽንኮቭናሰባት ሽጉጦችና  ሌሎች  የጦር መሣሪያዎችን በቁጥጥር ሥር ውለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም