በያቤሎ ከ1 ሺ 200 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን አደንዛዝ እጽ ተያዘ

68

ሚያዝያ 10/2011 ከመሀል ሀገር ወደ ሞያሌ ሲጓጓዝ የነበረ ካናቢስ የተባለ አደንዛዝ እጽ መያዙን  በሞያሌ ገቢዎችና ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስተባባሪ አስታወቁ፡፡

አስተባባሪው  ኢንስፔክተር አለሙ ይመር እንደገለጹት  አደንዛዝ እጹ የታየዘው ትናንት  በያቤሎ ገቢዎችና ጉምሩክ በመቆጣጠሪያ ሰራተኞች በተደረገ ፍተሻ ነው፡፡

አደንዛዝ እጹን ሲያጓጓዝ የተያዘው የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 -  57519 ኢት ሲኖ ትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ  ከስር   ለመንገድ ስራ አገልግሎት የሚውል ጠጠር በመጫን ተሸሽጎ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሽከርካሪውና  ረዳቱ  ለጊዜው ቢሰወሩም ክትትል እየተደረገ እንደሆነ ኢንስፔክተር አለሙ  አስታውቀዋል፡፡

በመቆጣጠሪያ ጣቢያው ሰራተኞች ፍተሻ የተያዘው ይሄው አደንዛዝ እጽ 5 ሚሊዮን  ብር  የሚገመት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ወርም በተመሳሳይ   በተደረገ ፍተሻ በርካታ ካናቢስ የተባለ አደንዛዝ እጽ መያዙን ከአስተባባሪው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ኢንስፔክተሩ እንዳሉት በህግ የተከለከለ አደንዛዝ እጽ ሲያዘዋውር የተገኘ ከአምስት ዓመት  በሚበልጥ እስራትና በገንዘብ ያስቀጣል፡፡

የያቤሎ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ህገወጥ እንቅስቃሴን ለመከላከል ከፌደራል ፣ከኦሮሚያና ከነዋሪው ህዝብ ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሆነም  አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም