በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ፖሊስ በጠየቀው የምርመራ ጊዜ ክርክር ተካሔደ - ኢዜአ አማርኛ
በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ፖሊስ በጠየቀው የምርመራ ጊዜ ክርክር ተካሔደ
ሚያዝያ10/2011በአቶ ሽመልስ ገብረስላሴ መዝገብ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ሽመልስ ገብረስላሴ፣ አቶ እንድሪስ ሙክታር፣ አቶ ታከለ ጉታ ፣አቶ ጌቱ አየለ፣ አቶ ሲሳይ ከፍያለውና አቶ ምናሉ ምትኩ ናቸው።
ተጠርጣሪዎቹ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ሲቀርቡ ፖሊሰ የማጣራት ስራዎች ስለሚቀሩኝ ተጨማሪ ጊዜ ይፈቀድልኝ ብሎ በመጠየቁ ነው።
የተከሳሽ ጠበቆች ግን ፖሊስ ላለፉት ሶስት ወራት ምርመራ ሲካሔድ እንደነበር የፌዴራል አቃቤ ሕግ የገለፀ በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜው ሊፈቀድለት አይገባም ብለዋል።
1ኛ ተከሳሽ አቶ ሽመልስ ገብረስላሴ በዝርዝር ፈጽመዋል በተባለው ወንጀል ፖሊስ ያስቀመጠው አለመኖሩን፣ በ6ኛ ተከሳሽም ላልተሰራበት 15 ቀናት ክፍያ ፈፀመዋል መባሉ የትኛው 15 ቀናት መሆኑን የሚጠቁመው ነገር የለም በማለትም ጠበቆቹ አንስተዋል።
ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን ቃል ለመቀበል፣ የፎረንሲክ ምርመራ ለማካሔድ፣የኦዲት ሪፖርት ለመቀበልና መረጃዎችን ለማገናዘብ በሚል ያቀረበው ማመልከቻ አግባብነት የሌለውና ጊዜ የማይጠይቅ ሲሆን ተጠርጣሪዎችን በእስር ለማቆየት ያለመ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም እነዚሁ ስራዎች የሚካሔዱት በመንግስት መስሪያ ቤቶች በመሆኑ ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና ቢወጡ ምርመራን ለማደናቀፍ የሚችሉበት መንገድ እንደሌለም አስረድተዋል።
ፖሊሲ በበኩሉ ምንም እንኳን ምርመራው ከሶስት ወር በፊት ቢጀመርም ስራው በሚስጥራዊነት ከተባባሪ አካላት ሲሰባሰብ ነበር ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በተለይ ማስረጃን የማስተርጎም ስራ በሶስተኛ ወገን የሚካሔድና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው በመሆኑ፤ በአብዛኛው በወቅቱ የነበሩ ኦዲተሮች መስሪያ ቤቱን በመልቀቃቸው የእነሱን ዝርዝር ቃል ለመቀበል ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ነው የጠየቀው።
በአሁኑ ወቅት በምርመራው ላይ በተሳተፉ የተለያዩ ተባባሪ አካላት ላይ ተጽኖ የማድረግ ሁኔታ በመኖሩ እንዲሁ እስካሁን ያልተያዙ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ስላሉ ተጠርጣሪዎች በዋስትና ቢወጡ ማስረጃዎችን ሊያጠፉ ይችላሉ ብሏል።
ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የፈፀሙት እርስ በእርስ በመመሳጠር በመሆኑ በዋስትና ቢለቀቁ በምርመራ ስራው ላይ ችግር ስለሚፈጥሩ ጥያቄውን ውድቅ እንዲያደርገው መርማሪ ፖሊስ ጠይቋል።
የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱም ፖሊስ እስካሁን ሲያካሒደው የነበረውን የምርመራ መዝገብ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ሰጥቷል።