ቀጥታ፡

ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው ለመመለስ የመንግስትን ጥረት መደገፍ ይገባል... የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር

ሚያዝያ  10/8/2011  ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው ለመመለስ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ገለጸ።

ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው ለመመለስ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ገለጸ።

ማህበሩ በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ድጋፉን ለተፈናቃይ ወገኖች ያስረከቡት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ፀሐፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ ባለፉት ጥቂት ወራት ከ38 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በአገር ደረጃ ከ240 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በጌዴኦ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች የተደረገው ድጋፍም የእዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዜጎች በመፈናቀላቸው በተለይ ህጻናትና እናቶች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ገልጸው በሀገር ደረጃ የተፈናቀሉትን ለማቋቋም ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ማህበሩ ይህንን የመዋለ ንዋይ ፍላገት በተወሰነ መልኩ በመጋራት ከመንግስት ጎን ለመቆም አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

"የመፈናቀል አደጋ ተከስቶ ሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ችግሩ ሳይከሰት በፊት ሰላምና መቻቻል ላይ በትኩረት መስራት ይገባል " ብለዋል፡፡

ዶክተር መሸሻ እንዳሉት በሀገር ደረጃ ተፈናቅለው ሰብዓዊ ድጋፍ ከሚፈልጉ ዜጎች በተጨማሪ ከ8 ሚሊዮን የሚበልጡ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ይፈልጋሉ።

ይህም አጋር ድርጅቶችን ብቻ ሳይሆን የመንግስትን አቅም ጭምር ፈተና ውስጥ ስለሚከተው፣ ጫናውን ለመቀነስ መንግስት ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት ባለድርሻ አካላት ሊደግፉት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የቦርድ አባል አቶ እያሱ ኩምሳ በበኩላቸው "ማህበሩ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚደርሱ ችግሮችን ለመቀነስ እየሰራ ቢሆንም ሰው ሰራሽ አደጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል" ብለዋል፡፡

አገር ውስጥ ያለውን ሀብት በማሰባሰብ ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ጥረት እተደረገ ቢሆንም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አጋር ድርጅቶችና መንግስት በሚያቀርቡት ሰብዓዊ ድጋፍ የተፈናቀሉ ዜጎችን በቀጣይነት እየደገፉ ማቆየት ስለማይቻል የዜጎችን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጡ በኩል ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ተሾመ ታከለ በበኩላቸው ለ200 ሺህ ህጻናትና እናቶች ደረጃቸውን የጠበቁ መጠለያ ድንኳኖች፣ ለ25ሺህ ህጻናት አልሚ ምግብና ዘይት፣ የበቆሎ ዱቄት ለተፈናቃዮቹ ከተደረጉ ድጋፎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

"ድጋፎቹ በውድ ዋጋ ከውጭ የገቡ ናቸው" ያሉት አቶ ተሾመ በተለይ የህጻናትና እናቶችን ጉዳት ለመቀነስ ትኩረት መደረጉንና በአጠቃላይ ከ4 ሚለዮን ብር ባላይ ግምት ያለው ሰብአዊ  ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በጌዴኦ ዞን ጎቲቲ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙት ተፈናቃዮች በበኩላቸው አጋር ድርጅቶችና መንግስት በምግብ እና በጤና አገልግሎት እያደረጉላቸው ባለው ድጋፍ ኑሯቸውን እየመሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"ሰርተን የዕለት ጉርሳችንን ማግኘት የምንችል ዜጎች በመሆናችን መንግስት ከድጋፍ ተላቀን እራሳቸንን የምናስተዳድርበት መንገድ ይፍጠርልን ሲሉም" ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም