ቀጥታ፡

ሶስተኛው የክልሉ የባህል ሳምንት በግልገል በለስ ይካሄዳል

አሶሳ ሚያዝያ 10 / 2011 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሶስተኛው የባህል ሳምንት ከፊታችን ቅዳሜ  ጀምሮ እንደሚካሄድ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

ሳምንቱ “በመደመር ዘመን በማይሽረው አብሮነት!” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ጸሐይ ሞርካ ለኢዜአ እንዳሉት ሳምንቱ ከሚያዝያ 12 እስከ 21 / 2011 በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ይደረጋል፡፡

ሳምንቱ የክልሉ ብሄረሰቦች ባህላቸውን በማስተዋወቅ አገራዊ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ታልሞ መዘጋጀቱን አመልክተዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ብሄረሰቦች ባህላዊ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ የመገልገያ ቁሳቁሶችና ዕደ-ጥበባት ፌስቲቫል እንደሚኖር ኃላፊዋ ገልጸዋል።

እንዲሁም ጥንታዊ ቅርሶችና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉብኝት ይደረጋል፡፡

በተጨማሪም ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት የሚካሄድ ሲሆን፤ የመጻህፍት ምረቃና የእውቅና ሽልማት እንደሚኖር ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም