በኳታር በህክምና የቆየችው ወይዘሮ ሜሮን ወደ አገሯ ተመለሰች

66

አዲስ አበባ ሚያዚያ 10/2011 ላለፉት 8 ዓመታት በኳታር በህክምና ላይ የቆየችው ወይዘሮ ሜሮን መኮንን ወደ አገሯ ተመልሳለች፡፡

በኳታር በደረሰባት በጭስ የመታፈን አደጋ ጉዳት ደርሶባት ላለፉት ስምንት አመታት በሀማድ ሆስፒታል በህክምና ላይ የቆየችው ኢትዮጵያዊት ወይዘሮ ሜሮን መኮንን ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ ወደ አገሯ ተመለሰች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች በቦሌ አለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ለወይዘሮ ሜሮን አቀባበል ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሜሮን ወደ አገሯ የተመለሰችው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መጋቢት 2011 ዓ.ም በኳታር ባደረጉት ጉብኝት ለአገሪቱ መንግስት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ሜሮን በአስቸኳይ ወደ አገሯ እንድትመለስ ስምምነት ላይ በተደረሰው መሰረት ነው።

የኳታር መንግስት ሜሮን ከኳታር ወደ አዲስ አበባ የመጣችበትን ሙሉ የትራንስፖርት ወጪዋን የሸፈነ ሲሆን በአገር ቤት ለአንድ አመት መታከሚያ የሚሆናትን ወጪንም እንደሚሸፍን ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርግላትም በመግለጫው ተመልክቷል።

ወይዘሮ ሜሮን መኮንን በሀማድ ሆስፒታል በነበራት ቆይታ በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲና በአገሪቱ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ክትትልና ድጋፍ ሲደርግላት መቆየቷንም ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም