ቀጥታ፡

ትዉልዱ የግድቡን ግንባታ በማጠናቀቅ አሻራ ማሳረፍ ይገባዋል-የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

ሆሳህና ሚያዝያ 09/2011 የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ንግድ ግንባታ በማጠናቀቅ ትዉልዱ አሻራውን እንዲያሳርፍ የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመለከቱ፡፡

ምሁራኑ ለኢዜአ ግድቡን እየተሳተፈ ያለው ትውልድ ለአገሩ ልማት አስተዋጽኦ ያለውን ግንባታውን ከዳር በማድረስ ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።ያስጀመረውን ግንባታ በማጠናቀቅም ታሪክ ማስመዝገብ ይጠበቅበታል።

በዩኒቨርስቲው የቋንቋና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል መምህር ኬራላ ናስር የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያውያን አንድ ያደረገውንና ንቅናቄ የፈጠረውን ታሪካዊው ግድብ ግንባታ ከዳር ማድረስ ይጠበቅበታል ይላሉ፡፡

ግድቡ ኢትዮጵያዉያን በራሳችን አቅም መሥራት እንደምንችል ያሳየንበት ፕሮጀክት በመሆኑም ግግንባታውን በማስፈጸም  ትውልዱ አሻራውን እንዲያሳርፍና ታሪክ ነጋሪ ብቻ ሳይሆን፤ ታሪክ ሰሪ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገው ተሳትፎ  ማጠናከር እንደሚገባውም  አመልከተዋል፡፡

በግላቸው ለግድቡ ግንባታ በሦስት ዙሮች ቦንድ እንደገዙ የተናገሩት መምህር ኬራላ፣ በዚህም ለልጆቻቸው ቅርስ እንዳስቀመጡ  ያህል ሆኖ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡

ግድቡ የአገሪቱን ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም ከማሳደግ አልፎ ለሌሎች አገሮች ኃይል በመሸጥ በመስጠት ተጠቃሚ ያደርጋታል ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲዉ የስፖርት ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር መሐመድ አወል ናቸው፡፡

የፕሮጀክቱ አስጀማሪ መላው ኢትዮጵያውያን በግድቡ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በማለፍ ታሪክ ማስመዝገብ ይገባዋል ሲሉም  አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

መንግሥት የግድቡን ግንባታ ሂደት ለኅብረተሰቡ በግልጽ በማሳወቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ ማስቀጠል አለበት ብለዋል፡ በግላቸውም የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መሐመድ አማን በበኩላቸዉ የግድቡ ግንባታ ''ይቻላል''የሚለዉን መንፈስ ያንጸባረቀ መሆኑን ይገልጻሉ።

ግንባታው ሥራ አጥነትን በመቀነስና ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ኃይል በማቅረብ የኢኮኖሚ ልማትን ለማፋጠን እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜና ወጪ ባለመጠናቀቁ የፈጠረውን ቅሬታ በመፍታት ተሳትፎውን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 66 ከመቶ ያህል ተጠናቋል።

ለግንባታውም እስካሁን ከ98 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።

ግድቡን በአራት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱ በቅርቡ መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም