ቀጥታ፡

ተፈናቃዮችን በአንድ ወር ጊዜ ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ

ዲላ ሚያዝያ 09/2011 መንግሥት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው ለመመለስ እየሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የተፈናቃይ አስመላሽና የመልሶ ማቋቋም ግብረ ኃይል፣ የጌዴኦ ዞን አመራሮችና የተፈናቃይ ተወካዮች በምዕራብ ጉጂ ዞን ተፈናቃዮችን ለመመለስ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት ተመልክቷል፡፡

የግብረ ኃይሉ አስተባባሪ አቶ ሚጣ ሚቻ  እንዳስረዱት መንግሥት ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው ለመመለስ አንድ ወር  ጊዜ መርሐ ግብር አውጥቶ እየሰራ ነው፡፡

በዚህም በቀጣይ ቀናት ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው መመለስ እንደሚጀመርም ተናግረዋል፡፡

መርሐ ግብሩን ለማስጀመር በምዕራብ ጉጂ ዞን ከቀርጫና ከብርብርሳ ኮጆ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ውይይት መደረጉንና ወረዳዎቹ የጸጥታ ችግር እንደሌለባቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የመልሶ ማቋቋምና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር  ትኩረት እንደሚሰጥ አስተባባሪው አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ለጊዜያዊ መጠለያዎች መስሪያ የሚያስፈልግ ቁሳቁስ በዚህ ሳምንት ወደ ሥፍራዎቹ  እንደሚልክም ገልጸዋል፡፡

የምዕራብ ጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አቶ አዱላ ህርባዬ በበኩላቸው  ተፈናቃዮችን ለመቀበል ከሕዝቡ ጋር  መወያየቱን አስታውቀዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው ሲመለሱ በጊዜያዊነት የሚጠለሉባቸው ሥፍራዎች ዝግጅት ኅብረተሰቡን በማስተባበር በመከናወን ላይ እንደሚገኝን አመልክተዋል፡፡

በዞኑ ምንም አይነት የጸጥታ ስጋት ሳይኖር ዜጎች በአሉባልታ ተደናግጠው መሰደዳቸውን የገለጹት ምክትል አስተዳዳሪው፣ ኅብረተሰቡ አንድነቱን በማስጠበቅ ችግር ፈጣሪዎችን እንዲታገላቸውን ጠይቀዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ መኮንን ጭጩ በበኩላቸው ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው መመለስ አሁን ካሉበት አሳሳቢ ሁኔታ ለማውጣት የሚደርስባቸውን ጫና እንደሚቀንስላቸው አመልክተዋል።

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋምና የደህንነት ስጋትን ለመቀነስ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ከተፈናቃዮቹች መካከል አቶ ኤዴማ ቡኖ ''በምዕራብ ጉጂ ዞን ተዘዋውረን ያየነው ነገር ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ወደ ቄያችን ተመልሰን ሰላማዊ ኑሮአችንን ለመጀመር ዝግጁ ነን'' ብለዋል፡፡

 መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ በተለይም በምሽትና በማሳቸው ውስጥ የሚደርስባቸው ጥቃትና ማስፈራራት እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡

የጸጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ከሆነ ያለ ምንም የመንግሥት ድጋፍ ዳግም የቀድሞ ሕይወታችንን መምራት እንጀምራለን ሲሉም ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ 270ሺህ ያህል ተፈናቃዮች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም