ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በኖርዌይ ይፋ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በኖርዌይ ይፋ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 27/2010 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በኖርዌይ ጉብኝት ለማድረግ ኦስሎ ገብተዋል። ሚኒስትሩ ኦስሎ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በስዊድን የኢትዮጵያ አምባሳደር ፕሮፌሰር መርጋ በቃና አቀባበል እንዳደረጉላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስ ኤሪክሰን ሶሪይዴ ጋር በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። በተጨማሪም ዶክተር ወርቅነህ ከኖርዌይ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮችና መከላከያ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ከያራ ኢንተርናሽናል ስራ አስኪያጅ እንዲሁም ከኖርዌይ ቢዝነስ ልዑክ ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ከኖርዌይ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የምታከናውነው ስዊድን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል። የኖርዌይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስ ኤሪክሰን ሶሪይዴ ባለፈው ጥር ወር በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር የተወያዩ ሲሆን አገራቱ በጋራ ተጠቃሚነትና አለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ለመስራት መስማማታቸው የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያና ኖርዌይ እ.ኤ.አ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ጠንካራ ወዳጅነት የነበራቸው ቢሆንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በይፋ የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1995 ነው። ኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር ከምትላቸው አገራት አንዷ ኖርዌይ ስትሆን በትምህርት፣ በዘላቂ ልማት፣ በምግብ ዋስትና እና በሰብአዊ ጉዳዮች ለኢትዮጵያ ድጋፍ ታደርጋለች። በተጨማሪም ሁለቱ አገራት በአካባቢ ጥበቃና ሃይል ልማት ዘርፍ ያላቸው ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይገኛል። ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ኦስሎ ከኦስሎ አዲስ አበባ በረራ የጀመረ ሲሆን ይህ መሆኑ የሁለቱን አገራት የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር እያጠናከረው መጥቷል። የሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ መጠንም ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።