ቀጥታ፡

ባንኩ ለሶማሌ ክልል ተፈናቃይ ዜጎች ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

ሚያዚያ 9/2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሶማሌ  ክልል ተፈናቃይ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍና መልሱ ማቋቋሚያ እገዛ የሚውል ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ  ዛሬ ለክልሉ መንግስት አስረከበ።

የድጋፍ ገንዘቡን ከባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና የተረከቡት የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር አቶ ሙስተፌ ሙሑመድ ዑመር ናቸው።

የባንኩ ፕሬዚዳንት በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ባንኩ ከብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን  ያገኘውን ከየክልሎቹ የተፈናቀሉ ዜጎችን ቁጥር መሰረት በማድረግ ለተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች  የገንዘብ ድጋፉን ክፍፍል አካሄዷል።

ለሁሉም ተፈናቃይ ዜጎች ድጋፍ እንዲውል ባንኩ  ከወሰነው 100 ሚሊየን ብር ውስጥ ለሶማሌ ክልል የሚደርሰውን  35 ሚሊየን አንድ መቶ ስልሳ ሰባት ሺህ ብር አስረክበዋል።

እንዲሁም ባንኩ በሀገሪቱ የጤናና ትምህርት ለማሻሻል 170 ሚሊየንብር መድቦ    የሶስት ጤናተቋማት  ግንባታ
እያካሄደ መሆኑንም አመልከተዋል፡፡ 

የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር አቶ ሙስተፌ ሙሀመድ በበኩላቸው  ባንኩ ላደረገው ድጋፍ በክልሉ መንግስትና ተፈናቃዮች ስም አመስግነዋል፡፡

ባንኩ በብድር አሰጣጥ ከክልሉ ህዝብ ባህልና እምነት ባገናዘበ መልኩ እንዲስተካክል በማድረግ የብድር  ተጠቃሚ እንዲያደርግም  ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲውል የወሰነው 100 ሚሊዮን ብር  ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣  ደቡብ፣ አማራ፣  ትግራይ፣ ቤኒሻንጉልጉሙዝ፣  ጋምቤላ እና ሐረሪ  ክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር  ለሚገኙ የሚውል መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም