በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር ለመፍታት በትብብር ይሰራል-ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር ለመፍታት በትብብር ይሰራል-ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 09/2011 በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር ለመፍታት ከባለድርሻዎች ጋር በትብብር እንደሚሰራ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በዘርፉ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር ለመፍታት በሚያስችል ብሄራዊ የጥራት መሰረተልማት ማሻሻያ ፕሮጀክት ዙሪያ ከጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ እንደተነሳውም ፕሮጀክቱ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በቆዳና ሌጦ እንዲሁም በጨርቃጨርቅና አልባሳት የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት ከዓለም ባንክ በተገኘ የ50ሚሊዮን ዶላር ብድር የሚተገበር ነው።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዮሃንስ ድንቅአየሁ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የሀገሪቱ እድገት እየጨመረ ሲመጣና የምታመርታቸው ምርቶች ወደ ውጭ ሀገራት በስፋት የመግባት እድል ሲያገኙ የምርትና አገልግሎት ጥራት ደረጃንም ማሳደግ ይገባታል ነው ያሉት።
ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ያሉት ምርቶችና አገልግሎቶች የጥራት መጓደል እየታየባቸው መሆኑ የምርቶቹ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትና የሀገሪቱን ኢንደስትሪ ለማዘመን በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያደርግ በመግለጽ።
በሀገሪቱ የሚመረቱ ምርቶች ዓለምአቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲመረቱና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ፕሮጀክቱ መቀረፁን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የምርምርና ፍተሻ ላብራቶር ዳይሬክተር ደምሌ አስራቴ በበኩላቸው በዘርፉ ጥራትን ለማረጋገጥ በአለም አቀፍ የጥራት ደረጃ መሰረት ስራዎች መከወን እንዳለባቸውና ስራውን የሚከውኑ ባለሙያዎችም የሰለጠኑና ብቃት ያላቸው መሆን እንዳለባቸው ይናገራሉ።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲሆንም በዘርፉ እውቅና ያላቸው ምርቶችን በማምረት ለዓለምአቀፍና ለሀገር ውስጥ ገበያው እንድናቀርብ ያግዘናልም ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ዓላማ የኢትዮጵያን ጥራት መሰረተልማት ወደ አለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ማድረግ ነው ያሉት ደግሞ የብሄራዊ የጥራት መሰረተ ልማት ማሻሻያ ፕሮጀክት የግል ዘርፍ ባለሙያ አቶ አባተ አርጋው ናቸው።
ፕሮጀክቱ በአምስት አመቱ ሲጠናቀቅ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ አለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን አምራቾች ቁጥር ከፍ በማድረግ ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሚላከውን የዘርፉን ምርት በ20 በመቶ ለማሳደግ ማለሙንም አስረድተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የጥራት ችግርን ለመፍታት ጥጥን የመሰሉ የጥሬ እቃዎች ጥራት እንዲሁም የመሳሪያ ግብአቶችና መለዋወጫዎች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አቶ አባተ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የጥጥን ጨምሮ ሌሎች የጥራት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ የጥራት ማረጋገጫ ለሚሰጡት የብሄራዊ ስነልክ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን ፅህፈት ቤትና የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ኤጀንሲ የመሳሪያ ድጋፍና የሰው ኃይል ስልጠና እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
በግሉ ዘርፍ በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በማር ምርት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቆዳና ሌጦ ማምረት ላይ ለተሰማሩ አምራቾችም የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ለፕሮጀክቱ ከተገኘው ብድር 38 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ለጥራት ድርጅቶች፣ 7ነጥን 3 ሚሊዮኑ ለግሉ ዘርፍ አምራቾች ቀሪው ደግሞ ስራውን ለማስተዳደር እንደሚውልም ተነግሯል።
ፕሮጀክቱ እ.አ.አ በ2017 ላይ የተጀመረ ሲሆን በ2022 የሚጠናቀቅ መሆኑም ተገልጿል።