ቀጥታ፡

የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ ባቡሩ በየጣቢያው የሚደርስበትን ጊዜ 10 ደቂቃ ለማድረግ ጥናት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ሚያዝያ 09/2011 34 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ፕሮጀክት የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ ባቡሩ በየጣቢያው የሚደርስበትን ጊዜ 10 ደቂቃ ለማድረግ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ገለጸ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት መስከረም 2008 ዓ.ም ጀምሮ በተገልጋዩ ዘንድ ቅሬታ ይነሳበታል።

ኮርፖሬሽኑም ህብረተሰቡ የሚያነሳውን ቅሬታ ተቀብሎ ለማስተካከል እርምጃ እየወሰደ ቢሆንም በሚፈለገው ፍጥነት አለመሄዱን ገልጸዋል።

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በተደረገ ተቋማዊ ግምገማ ባቡሮች በየጣቢያው የሚደርሱበትን ሰዓት 12 ደቂቃ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

ኢዜአ በጣቢያዎቹ ተገኝቶ ባደረገው ማጣራትም ባቡሮች ከ12 እስከ 15 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚመጡ አረጋግጧል።

ከሃያት አደባባይ ጦር ኃይሎች ድረስ ባለው መስመር ከታህሳስ አጋማሽ ጀምሮ፣ ከቃሊቲ እስከ ምኒሊክ አደባባይ ድረስ ባለው መስመር ደግሞ ከመጋቢት ወር ጀምሮ የባቡሮች መምጫ ሰዓት 12 ደቂቃ መደረጉን ያነሳሉ ዶክተር ስንታየሁ።

የባቡሮቹ በየጣቢያው የመድረሻ ሰዓት 12 ደቂቃ በመሆኑም የመጣውን ውጤት በመገምገም ሰዓቱን ለማሻሻል የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ስንታየሁ፤ ወደ 10 ደቂቃ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የባቡር ካፒቴኖች አሁን ተግባራዊ በተደረገው ጊዜ መሰረት እየተለማመዱ የተሻለ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የ10 ደቂቃው ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

ጥቅምት 29 ቀን 2011 ዓ.ም የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ዋና መስሪያ ቤት የቃሊቲ ዴፖ የስራ እንቅስቃሴን ሲጎበኙ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡሮች በሙሉ አቅም ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸው ይታወሳል።

በትራንስፖርት ሚኒስቴር የ100 ቀናት እቅድ ውስጥም አንድ የባቡር ተሳፋሪ በባቡር ጣቢያ ባቡር ለማግኘት የሚጠብቅበትን የ15 ደቂቃ ጊዜ ወደ12 ደቂቃ ዝቅ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ መናገራቸው ይታወቃል።

በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ለተሳፋሪዎች የሚያገለግሉ 41 ባቡሮች ቢኖሩትም በአገልግሎት አሰጣጣቸው በህብረተሰቡ ቅሬታ ይነሳባቸዋል።

ባቡሮቹ በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እንዳይሰጡ ከሚያደርጉ ዋነኛ ምክንያቶች ደግሞ አንዱ ባቡሮቹ ሲበላሹ ቻይና ወስዶ ጥገና ለማድረግ የሚወስደው ጊዜ መሆኑን በመገንዘብ ኮርፖሬሽኑ ከቻይና መንግስት ጋር በመነጋገር የባቡር ጥገና ማዕከል ግንባታ ለማካሄድ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኝ ታውቋል።

የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የሚገኘው ገቢና ወጪ አለመጣጠን፣ የመለዋወጫ እቃዎች በበቂ ሁኔታ አለመገኘትና ለዕቃዎች ግዢ በቂ የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ አለማግኘት የአገልግሎቱ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው።

ባቡሮቹ በየጣቢያው የሚደርሱበት ጊዜ 30 ደቂቃና ከዚያ በላይ የነበረ በመሆኑ በርካታ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ህብረተሰብ ያማርር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁን መሻሻል ማሳየቱ ጥሩ ሆኖ ከዚህም በላይ መሻሻል እንደሚገባው ብዙዎች ያነሳሉ።

በተለይም በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የባቡሮቹ በሮች መዘጋት እስኪያቅታቸው ድረስ ከፍተኛ መጨናነቅ ያጋጥማቸው እንደነበርም እንዲሁ።

በተገኘው መረጃ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በአሁኑ ወቅት በቀን ከ115 እስከ 120 ሺህ ሰዎችን ያጓጉዛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም