ቀጥታ፡

የምርጫ ቦርድ ዳግም መዋቀር ለዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ተስፋ አጭሯል

ሚያዝያ 9/2011የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ዳግም ለማቋቋም አዋጅ መጽደቁ ለዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ተስፋ የሚያጭር መሆኑ ተነገረ።

የአዋጁ መውጣት ብቻ ሳይሆን በትክክል ስራ ላይ መዋል ተጨባጭ ለውጥእንደሚያመጣም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የዲሞክራሲና የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴ በአደረጃጀትና ሌሎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ቁርጠኛ አቋም መያዙን ገልጿል።

ይህን አቋም ተግባራዊ ካደረገባቸው አንዱ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሲሆን በአደረጃጀት ችግር በህዝብና በፖለቲካ ፓርቲዎች ተዓማኒነቱንና ተቀባይነቱን አጥቶ መቆየቱን በቅርቡ የጸደቀው የቦርዱ ማቋቋሚያ አዋጅ ያወሳል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመስኩ ምሁራንና የመንግስት የስራ ኃላፊዎችም የቦርዱ እንደገና መቋቋም አስፈላጊነት ገልጸው፣ አዋጁ ወጥቶ ተግባር ላይ እንዲውል ሊሰራ እንደሚገባ ያሳስባሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህር ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው አሰፋ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል ምርጫዎችን ሲያስፈጽም የተለያዩ ቅሬታዎች ይነሱ እንደነበር ያስታውሳሉ።

 በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቦርዱ ገለልተኛ ባለመሆኑ "ስልጣን ላይ ላለው ፓርቲ ያደላል" በሚል ተሳትፏቸው ትርጉም እንዳሌለው በስፋት ቅሬታ ያነሱ ነበር ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ምርጫ ቦርድ የዴሞክራሲ ግንባታ ተቋማት ከሚባሉት አንዱና ዋነኛው በመሆኑ እነዚህን ችግርች ለመፍታትና የቦርዱን ገለልተኛነት ለማረጋገጥ፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና ብቃቱን ለማሳደግ ዳግም እንዲዋቀር ማሻሻያ መደረጉ በትክክለኛው ሰዓት መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም ቀደም ሲል በነበረው አደረጃጀት ቦርዱ 9 አባላት ኖረውት በምርጫ ወቅት ብቻ ግማሽ ሰዓት ይሰሩ የነበሩ በመሆናቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ሌላ ባለጉዳይ በፈለገበት ጊዜ አገልግሎት ለማግኘት የሚቸገርበት አሰራር ነበር።

በአዲሱ የአደረጃጀት ህግ ቦርዱ 5 አባላት ብቻ ኖረውት አምስቱም ቋሚ ሆነው እንዲሰሩ ማስቀመጡ ማንም ባለጉዳይ በፈለገበት ጊዜ አገልግሎት እንዲያገኝ ስለሚያስችል ቅሬታዎችን ይቀንሳል ይላሉ።

የህግ ባለሙያው በአዲሱ አዋጅ ውስጥ የተካተቱት ነጥቦች ከወቅቱ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተገቢ መሆናቸውን በአጽእኖት ያስቀምጣሉ።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምርጫ ቦርድ ዳግም እንዲዋቀር መደረጉ በ2012 ዓ.ም የሚደረገው ምርጫም ፍትሃዊና ገለልተኛ እንዲሆን እንደሚያስችልም ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ሳሳሁልህ ከበደ አሁን ባለው አሰራር ከላይ ያለው አደረጃጀት የተሻለ ቢሆንም ወረዳ ላይ ካልተሰራ ችግሩ አሁንም ሊቀጥል እንደሚችል በማንሳት ከወዲሁ ትኩረት እንዲደረግ ይመክራሉ።

የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ኡመር መሃመድ በበኩላቸው ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሃሳብ ያላካተተ እንደነበር እና አሁን የጸደቀው አዋጅ በዚህ እንደሚለይ በማንሳት አፈጻጸሙ ላይ ትኩረት እንዲደረግ ያነሳሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከተጽእኖ ነጻ መሆን ካለባቸው ተቋማት አንዱ ምርጫ ቦርድ ነው የሚል ሃሳብ አላቸው።

ሰብሳቢዋ አዲሱ ማቋቋሚያ አዋጅ ቀደም ሲል ቦርዱ ነጻና ገለልተኛ ባለመሆኑ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት አዳዲስ ድንጋጌዎች የተካተቱበት በመሆኑ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነትም አላቸው።

ወይዘሪት ብርቱካን ቦርዱ የመንግስት ሰራተኛ መመሪያን ሳይጥስ በራሱ መስፈርት ሙያተኞችን መቅጠር እንደሚችልና በበጀት ላይም ወደ አስፈጻሚው ሳይሄድ ሙሉ ስልጣን እንደሚኖረው ከሚያስቀምጡ አዳዲስ ድንጋጌዎች ውስጥ ጠቅሰዋል።

አዋጁ ነጻና ገለልተኛ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን በመጥቀስ ሌሎች ተግባራዊ የሚሆኑ የማሻሻያ ሃሳቦች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ፍትሃዊ፣ ገለልተኛና ተአማኒ ምርጫ ማድረግ በቦርዱ ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ መንግስት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ዜጎችም የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንደሚኖርባቸው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማቋቋሚያ አዋጅ ጠንካራ፣ ገለልተኛና ተአማኒ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ለማደራጀት ምቹ የሆኑ የህግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ ለማድረግ ያለመ መሆኑም በአዋጁ ተደንግጋል።

ይህንንም ለማረጋገጥ ቦርዱን እስከ ወረዳ ድረስ መልሶ የማደራጀት ተግባር በጥናት ላይ ተመስርቶ እየተሰራ መሆኑን ሰብሳቢዋ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም