እንደ አገር ከሚለያዩን ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራትይገባል- ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ - ኢዜአ አማርኛ
እንደ አገር ከሚለያዩን ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራትይገባል- ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 9/2011 እንደ አገር ከሚለያዩን ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።
እንደ አገር ከሚለያዩን ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።
አስተዳደሩ በከተማዋ መሃል መዲና ለማስገንባት ባሰበው የአድዋ ድል የሚዘከር ሙዚየም አስመልክቶ የመነሻ ውይይትና ዲዛይን ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
ምክትል ከንቲባው ኢንጅነር ታከለ ኡማ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት "አድዋ ለአገራችንና አፍሪካዊያን የሚያኮራ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ቢወራ፣ ቢፃፍና ቢተረክ የማይሰለች፤ ኢትዮጵያኖችን በጋራ ያስተሳሰረን ትልቅ የደምና የአጥንት ውጤት ነው"።
"አድዋ ስፍራ ብቻ ሳይሆን የእኛ ታሪክ፣ ማንነት፣ የአባቶቻችን ተጋድሎ ውጤት፣ የእኛ ኩራትና ለመጪው ትውልድና ለልጆቻችን ደግሞ እራሳቸውን የሚያዩበት የታሪክ መስተዋት ነው።"
"ለዚህ የታሪክ ክስተት፣ የፈተናዎች ሁሉ መጨረሻ፣ የጀግንነት ሁሉ ጫፍና ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀን ኃይል በኋላ ቀር የጦር መሳሪያ ማሸነፍ ለተቻለበት ፍልስፍና ማዕከል መገንባት ያስፈልጋል" ብለዋል።
በመሆኑም አስተዳደሩ ማዕከሉን ለማስገንባት ሚድሮክ ለ20 ዓመታት አጥሮ ይዞት በነበረውና በቅርቡ የተለቀቀው መሬት ላይ ማዕከሉን ለማስገንባት እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
የማዕከሉ ግንባታ ዓላማም መሬቱን ለባለሃብት ከመስጠትና ህንጻ ከመገንባት ይልቅ ዘመን ተሻጋሪ የሆነውን የአድዋን ታሪክ በማኖር ከሚለያዩን ነገሮች ላይ ጊዜ እያጠፋን ነገሮች ከእጅ እንዳይወጡ የሚያደርግ አስተሳሰብን በማስቀረት አንድ የሚያደርጉንን ቅርሶችና ታሪኮችን ለማኖር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህም ታሪክን ለመዘከር፣ የጋራ ሃውልቶቻችንን ልጆቻችን እንዲያዩት፣አባቶቻቸው የሰሩትን ተጋድሎ እንዲመለከቱና እንዲኮሩበት እንዲሁም የተዛባ ታሪክን እንዲያስተካክሉና ልዩነትን አጥብበው እንድ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያኖች ዋና ከተማ መሆኗን ጠቅሰው በሚገነባው የአድዋ ማዕከል ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት፣ጥሩ የሚሰራ ኩባንያ የሚመረጥበት፣ ለግንባታው የሚሆን ገንዘብና እውቀት አስተዋጾኦ የሚያደርግበት ይሆናልም ብለዋል።
የማዕከሉ ግንባታ ከቀለም፣ ከጎሳ፣ ከቋንቋና ከፖለቲካ አመለካከት ወጣ ብለን አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ ለመሳተፍ የመጀመሪውና ትልቁ አጀንዳ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ መስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቻው የሚገነባው የአድዋ ድል የሚዘክር ማዕከል ላይ ሁሉም ኢትዮጵያ እንዲሳተፍበት ይደረጋል።
በአድዋ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጾታ፣ቀለም፣ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለይ እንደተሳተፈ ሁሉ በግንባታው ሂደት ላይም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለውን ሀሳብ በማካተት ልዩነትን ለማሰቀረትና አባቶቻቸን በጋራ የሰሩት ገድል በጋራ እንዲካተት ይደረጋል ሲሉም ገልጸዋል።
ማዕከሉ የአድዋ ድል በዓመት አንድ ጊዜ ከማክበር በቋሚነት ዓመቱን ሙሉ የሚዘከርበት እንደሚሆን ጠቁመው ይህም ማዕከሉ ቱሪስቶች፣ መላው ኢትዮጵያዊያን፣ አፍሪካዊያንና ሌሎችም በመጎብኘት ስለ አገሪቷ እንድነት የሚሰሩትን ስራ እንዲያጠናክሩ ያስችላል ብለዋል።
የአድዋ ድል የሚዘከር ማዕከል አስመልክቶ የመነሻ ውይይትና ዲዛይን ያቀረቡት የዲዛይንና የስነ ጥበብ ባለሙያው አቶ አገኘው አዳነ በበኩለቻው የሚገነባው ማዕከል በአካበቢው ያሉትን በተለይም ታሪካዊ መዘጋጃ ቤቱን ህንፃ እንዳይውጥ ተደርጎ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
ማዕከሉ የሚገነባበት ቦታ የሀገሪቷ ከተሞች ርቀት መነሻ ቦታ ከሆነው 0.00 ኪሎ ሜትር በሆነው በጥንታዊ መጠርያው ሲኒማ አድዋ በመባል በሚታወቀው ቦታ ላይ ነው።
በውስጡም ጦርነት የታከሄደባቻው የጦር መሳሪያዎች፣በወቅቱ የነበረውን የምግብና ስንቅ ሁኔታ፣ልክ እንደ አባቶቻችን በባዶ እግር የሚኬድበት ቦታ፣የቲያትር ቦታ፣የማንበቢያ ቦታ፣ጋለሪ፣የህፃናት ማቆያ ቦታዎችንና የመሳሰሉትን የሚያካትት ይሆናል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሚገነባው የአድዋ ድል የሚዘክር ማዕከል በወቅቱ የነበሩትን ኹነቶች ሁሉ በማካተትና የትኛውም አካል ቅሬታ እንዳይሰማው ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
አባት አርበኛ ጌታቸው የተባሉ አስተያየት ሰጪ እንደገለጹት በወቅቱ ሃይማኖቶች የነበራቸው ሚና፣ዝግጅቶች፣የምርኮኞች ልወውጥና የጦርነቱ ሁኔታ በተገቢው ሁኔታ መካተት ይገባዋል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አርቲስት ደበበ እሸቱ እንደገለጸው ማዕከሉ ነፃነትን፣ፍትህን፣ በወቅቱ የነበረውን የሰዉን አኗኗር ሁኔታ፣የቤት አሰራር ወዘተ ያመከለ ቢሆን ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።
ውይይቱ በቀጣይም ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚካሄድ ሲሆን ማንም ሀሳብ አለኝ የሚል ሰው በሚከፈተው ድረ ገጽና በአካል አስተያየቱን ማቅረብ ይችላልም ተብሏል።