የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ከኢህአዴግ ምክር ቤት አገራዊ ለውጡን የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች እንጠብቃለን አሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ከኢህአዴግ ምክር ቤት አገራዊ ለውጡን የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች እንጠብቃለን አሉ
አሶሳ ሚያዚያ 08 / 2011 ከኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ አገራዊ ለውጡን የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች እንደሚጠብቁ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋረራቸው አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች እንዳመለከቱት አገራዊውን ለውጥ ወደፊት የሚያራምዱ ውሳኔዎች ከስብሰባው ይጠብቃሉ።ለዚህም የግንባሩ አባል ድርጅቶች መግባባት ወሳኝ ነው።
በአገሪቱ የተገኘውን ተስፋ ሰጪ ለውጥ ማስቀጠል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣አገርን የመምራት ኃላፊነት የተረከበው ድርጅት መሪነቱን የሚያሳይበት አጋጣሚ መፍጠር አለበት ይላሉ፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ አቶ አበበ በዳኔ የተባሉት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ኢህአዴግ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ እንደማይታማና አፈጻጸም ግን የዘመናት ችግር ሆኖ መዝለቁን ይገልጻሉ፡፡
“አሁን አገሪቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላም መመለስ በጉባዔው ተወሰነም አልተወሰነም አንገብጋቢ ጉዳይ ነው”ብለዋል።
ድርጅቱ በስብሰባው የሚወያይበትና እርምጃ ይወሰድበታል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ጥያቄዎቹን በዴሞክራሲዊ አካሄድ በማንሳት ለውጡን ለማራመድ አቅም መሆን እንደሚገባው መክረዋል፡፡
አቶ ዩሱፍ ሃሚድ የተባሉ ነዋሪ በአገሪቱ አንዳነድ ክፍሎች የሚታየውን የሰላም መደፍረስ ለመግታት ከስብሰባው ውሳኔዎች እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።
“አገር የምትጎዳው በብዙሃኑ ሳይሆን፤ በጥቂት አጥፊዎች ነው” ያሉት አቶ ዩሱፍ ፣በሕዝቡ በሚታይ ቸልተኝነትና ጉዳዩን ለመንግሥት ብቻ በመተው ችግሮች እንዳይባባሱ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለዚህም ሕዝብና መንግሥት ተግባብተው መሥራት እንደሚኖርባቸውም አመልክተዋል፡፡
አቶ መለሰ ምህረቱ ኢህአዴግ “አውራ እና አጋር” የሚለውን የተበታነ አካሄድ አስቀርቶ አንድ ሃገራዊ ፓርቲ ለመሆን የጀመረውን ጥረት እንደሚያደንቁና በተወሰነ ደረጃ በሀገሪቱ ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሄ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ከኢህአዴግ ውስጥ የወጣውን የለወጥ ኃይል የሚፈታተኑ ችግሮች ስብሰባውን እንዳያደናቅፉ መሰራት እንደሚገባው ይናገራሉ።
ለውጡን ለይምሰል የሚደግፉ በየክልሉ የሚገኙ አቅምን፣ ችሎታንና የፖለቲካ ብቃት መሠረት ያላደረጉ ሪፎርሞች ፈተና ሆነው እንደሚቀጥሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢሕአዴግ)ምክር ቤት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።