ቀጥታ፡

አቡጊዳ የቼስ ክለብ የኢትዮጰያ ቼስ ክለቦች ውድድርን አሸነፈ

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2010 ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የኢትዮጰያ ቼስ ክለቦች ውድድር በአቡጊዳ የቼስ ክለብ አሸናፊነት ተጠናቋል። ከግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ የነበረው ውድድር ትናንት ፍጻሜውን አግኝቷል። አቡጊዳ፣ቴራት፣ኢትዮ አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ፣አዲስ እና ቴራት በውድድሩ ላይ የተሳተፉ የቼስ ክለቦች ናቸው። የኢትዮጵያ ቼስ ፌደሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ እንዳሉት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ስፖርቱን ለማስፋፋት መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ለአምስት ቀናት በተካሄደው ውድድርም በአጠቃላይ የአቡጊዳ የቼስ ክለብ አሸናፊ ሆኗል። አቡጊዳ የቼስ ክለብ አሸናፊ በመሆኑ የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት ሲያገኝ ቴራትና ኢትዮ አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ በመውጣት የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በተጨማሪም በግል የበላይነት ውድድሮች አሸናፊ ለሆኑ ተወዳዳሪዎች የዋንጫና የሜዳሊያ ሸልማትም ተበርክቶላቸዋል። በወንድ ጾታ እና በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የተወሰነው የመጀመሪያው የቼስ ክለቦች ውድድር በቀጣይ በሁለቱም ጾታዎች ለማካሄድና ክልሎችን ለማሳተፍ ጥረት እንደሚደረግ አቶ ሰይፈ ጠቁመዋል። ክልሎች በውድድሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥያቄ ቢቀርብም በበጀት እጥረትና ክለቦቹ ባለመደራጀታቸው የተነሳ መሳተፍ እንዳልቻሉ አመልክተዋል። ፌደሬሽኑ ለክልል ቼስ ፌደሬሽኖች የቁሳቁስና የስልጠና ድጋፍ እያደረገ መሆኑንና በቀጣይ ክልሎች የቼስ ክለቦች ማደራጀት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ቼስ ከሁሉም የሰሌዳ ላይ ስፖርታዊ ጨዋታዎች መካከል ቀዳሚው ሲሆን፤ በአለም አቀፍ በተለይም በቤተ-መንግስት ደረጃ፣ በወታደራዊ መስክ በተሰማሩ ሰዎችና በምሁራን ዘንድ ተወዳጅና ተመራጭ ነው። ጨዋታው ነገሮችን በፍጥነት የመረዳት፣ በትኩረት የማሰብ፣ ቀጣይ ሊሆን የሚችለውን የመተንበይና ፈጣን የሂሳብ እውቀት የሚጠይቅ ሲሆን፤ በርካታ ፖለቲከኞችና የአገር መሪዎች ከሚያዘወትሯቸው ጨዋታዎች መካከልም ተጠቃሽ ነው። የቼስ ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ዘመናት ቢቆጠሩም እስካሁን ድረስ በብዙዎች ዘንድ የአስተሳሰብ ክፍተት መኖርና ስለ ስፖርቱ ጠቀሜታ በተገቢው ሁኔታ ባለመረዳት እድገቱ የእድሜውን ያህል አልፈጠነም። በተለይም የስፖርቱ መጫወቻ ቁሳቁሶች ዋጋ ውድ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በሁሉም አካባቢ ስፖርቱ እንዳይዘወተርና እንዳይታወቅ ምክንያት ሆኗል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም