በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ 10 አባላት ተመረጡ - ኢዜአ አማርኛ
በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ 10 አባላት ተመረጡ
አዲስ አበባ ግንቦት 27/2010 ትናንት በተካሄደው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ 10 አባላት ተመርጠዋል። የምርጫ ሂደቱ እስከ ምሽቱ 5 ሰአት የቆየ ሲሆን ስምንት ክልሎችና ሁለቱን ከተማ አስተዳድሮች የወከሉ 20 እጩዎች ተወዳድረዋል። የኦሮሚያ ክልል የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራን በማስመረጡ ምክንያት በስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ምርጫ እጩ ማሳተፍ ስለማይችል 10 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ ተመርጠዋል። በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ክልል የወከላቸው ዶክተር ኃይሌ ኢቲቻና አቶ ከማል ሁሴን በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ አልተሳተፉም። በተሰጠው ድምጽ መሰረት አቶ ሰውነት ቢሻው ከአማራ ክልል፣ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ከአዲስ አበባ፣ አቶ አበበ ገላጋይ ከድሬዳዋ፣ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ከደቡብ ክልል፣ ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ከትግራይ፣ አቶ አሊሚራህ መሐመድ ከአፋር፣ አቶ አብዱራዛቅ ሀሰን ከሶማሌ፣ አቶ ቻን ጋትኮት ከጋምቤላ፣ አቶ ኢብራሂም መሐመድ ከሐረሪና ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሆነው ተመርጠዋል። ከስምንቱ ክልልና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በኮታ አንድ አንድ ሰዎች ተመርጠዋል። ከአዲስ አበባ፣ ሐረሪና ጋምቤላ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት ሰዎች ያገኙት ድምጽ 50 ሲደመር 1 ባለመሆኑ በድጋሚ ምርጫ ተደርጎ የአዲስ አበባ፣ ሐረሪና ጋምቤላ ተወካዮች 50 ሲደመር 1 ድምጽ አግኝተው የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴው አባል ሆነው ተመርጠዋል ። አዲስ አበባን የወከሉት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫው እጩዎች ባላቸው የእግር ኳስ ልምድና ለእግር ኳሱ ባበረከቱት አስተዋጽኦ መሆን እያለበት በኮታ መሆኑ አግባብ አይደለም በሚል የምርጫውን አካሄድ በመቃወም ራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል። አሰልጣኝ አስራት በመጀመሪያው ዙር የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ላይ ተሳትፎ አድርገው ነበር። የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ ከተመረጡ በኋላ በተካሄደው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ምርጫ የኮሚቴው አባላት ከሆኑት ውስጥ ስድስቱ ተሳትፈዋል። አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ከደቡብ፣ አቶ አሊሚራህ መሐመድ ከአፋር፣ አቶ አብዱራዛቅ ሀሰን ከሶማሌና አቶ ኢብራሂም መሐመድ ከሐረሪ ክልሎች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታችን ብቻ ይበቃናል በሚል በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ምርጫ ራሳቸውን አግልለዋል። በዚህም መሰረት ስድስቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በተሳተፉበት ምርጫ የትግራይ ክልልን የወከሉት የቀድሞው የደደቢት ክለብ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም 44 ድምጽ በማግኘት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል። አቶ አበበ ገላጋይ ከድሬዳዋ 30፣ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ከአዲስ አበባ 27፣ አቶ ሰውነት ቢሻው 22 እና ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙን ከቤኒሻንጉል ጉምዝ 10 ድምጽ አግኝተዋል። ከጋምቤላ ክልል የተወዳደሩት አቶ ቻን ካትኮት በምርጫው ምንም ድምጽ አላገኙም። የተመረጡት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ለቀጣይ አራት ዓመታት በስራ ላይ የሚቆዩ ይሆናል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፈርህያ መሃመድና በአፋር ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአብዴፓ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሀሰን አብዱልቃድር ለክለቦችና ለክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ስጦታ በማበርከት የምርጫው ሂደት ተጠናቋል። ለረጅም ጊዜ ሲጓተት የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ መቋጫ አግኝቷል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ከዚህ በፊት አራት ጊዜ መራዘሙ ይታወሳል።