የወላይታ ዲቻ ቮሊይ ቦል ቡድን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
የወላይታ ዲቻ ቮሊይ ቦል ቡድን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸነፈ
ሶዶ ግንቦት 26/2010 ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም ቀጥሎ በተካሄደው የ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ የወንዶች ቮሊይ ቦል ጨዋታ የወላይታ ዲቻ ቮሊይ ቦል ቡድን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አቻውን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸነፈ። የወላይታ ድቻ የመጀመሪያ ሁለት ዙሮችን 25 ለ 22 እና 25 ለ 21 በሆነ ውጤት ቢያሸንፍም ሦስተኛውን ዙር በተጋጣሚው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 25 ለ 21 በሆነ ውጤት ሊጠናቀቅ በመቻሉ ጨዋታዉ ለ4ኛ ዙር ሊቀጥል ችሏል በ4ኛ ዙር ጨዋታ ባለሜዳው ተጋጣሚውን 25 ለ 18 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዕለቱን ጨዋታ ከማሸነፍም በላይ በሊጉ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ያለውን የነጥብ የበላይነት ሊያስጠብቅ ችሏል። በሁሉም የጨዋታ ዙሮች ሁለቱም ተጋጣሚዎች አሸናፊ ለመሆን ጠንካራ የፉክክር መንፈስ አሳይተዋል። የወላይታ ድቻ ቮሊይ ቦል ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሻምበል ጳውሎስ ሹኬ "ተጋጣሚያችን ከባድ መሆኑን ስለምናውቅ ለሻምፕዮናነት የምናደርገው ጉዞ እንዳይደናቀፍ በተላይ በስነ ልቦና ረገድ ያደረግነው ዝግጅት ለስኬታችን ቁልፍ ነበር" ብለዋል። "በአካል ብቃት የነበሩ ድክመቶችን በተገቢው እያረምን በመምጣታችንም የሚገባንን ነጥብ ልናገኝ ችለናል" ሲሉም ተደምጠዋል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቮሊይ ቦል ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኢንስፔክተር ብሩ መአ በበኩላቸው የተጨዋች ቅጣትና ጉዳት ቡድኑ በመጠኑ እንዲሳሳ ቢያደርግም የወላይታ ድቻ ቡድን ጠንካራ ቡድን ነው፤ ለመመከት ብንሞክርም በክፍተታችን ሊጠቀም ችሏል፤ ይገባዋል።" ብለዋል በቡድኑ ውስጥ በዕድሜ ምክንያት የሚለቁ ተጨዋቾች እንዳሉ ገልጸው በተላይ የዘንድሮ ውድድር የተጨዋች ስብስብን ከማጠናከር አንጻር ለሚቀጥለው የውድድር ዓመት እንዴት መዘጋጀት እንዳለባቸው ትምህርት ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል። በርካታ ደጋፊዎች በሜዳው ተገኝተው ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ ቡድኖቻቸውን አበረታትተዋል። በተመሳሳይ ዛሬ በአዲስ አበባ በመከላከያና መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ መካከል በተካሄደ ጨዋታ መከላከያ ተጋጣሚውን 3 ለ 1 በሆነ ተመሳሳይ ውጤት በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 15 ማሳደግ ችሏል። ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ዕድሜ የቀረውን የዘንድሮ ቮሊይ ቦል ውድድር ወላይታ ድቻ በ28 ነጥብ ሲመራ መከላከያ፣ ሙገር ሲምንቶና ጣና ባህር ዳር እያንዳንዳቸው በ15 ነጥብ ይከተላሉ።