የትራንስፖርት ሥርአቱን ለማሻሻል በ300 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተሰራ ነው

35
ደብረ ብርሃን ግንቦት 27/2010 በአገር አቀፍ ደረጃ የትራንስፖርት ሥርአቱን ለማሻሻል በ300 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ። የመንገድ ደህንነትን አስመልክቶ የተዘጋጀው ዞን አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል። የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሸን ዳይሬክተር አቶ ይግዛው ዳኛው ለኢዜአ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ከተያዘው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ እየተተገበረ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚውለው ገንዘብ ከዓለም ባንክ በብድር የተገኘ ነው። "በብድር በተገኘው ገንዘብ በአገር አቀፍ ደረጃ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችል የተሽከርካሪ ምዝገባ ለማካሄድና የምርምራ ሥርአቱን ለማሻሻል የሚውል ነው" ብለዋል። በተጨማሪም ገንዘቡ በአገር አቀፍ ደረጃ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ሥርአትን ለማሻሻል እንደሚውል አስረድተዋል። ወጥ የሆነ የቅጣት አወሳሰን ሥርአት ለማስፈን የሚያስችል ዳታ ቤዝ እንደሚደራጅም ነው አቶ ይግዛው ያመለከቱት። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ለፕሮጀክቱ ከተመደበው አጠቃላይ ገንዘብ ወስጥ 192 ሚሊዮን ዶላሩ በአዲስ አበባ ያለውን የትራንስፖርት ሥርአት ለማሻሻል የሚውል ነው። ቀሪው 107 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ፣ የተሽከርካሪ ምዝገባና ምርመራ፣ የትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝ እንዲሁም የተቀናጀ የመንገድ ትራፊክ ቅጣት አስተዳደር ሥርአቶችን ለማሻሻል እንደሚውል አስረድተዋል። እግረኛና አሽከርካሪ አጥፊዎች የሚዳኙበት ነባር አዋጅና ደንቦችን የማሻሻል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው "ይህም ሥራ ላይ ሲውል 85 ከመቶ በአሽከርካሪዎች ስህነ ባህሪ ምክንያት ይደርስ የነበረውን ጥፋት ለማስቀረት ያግዛል" ብለዋል። አቶ ይግዛው እንዳሉት ከታህሳስ 2009 ዓ.ም ጀምሮ” ከትራፊክ አደጋ የፀዳ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሀገራዊ ሕዳሴ" በሚል መሪ ቃል የህዝብ ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው። በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻዲቅ በበኩላቸው የምክክር መድረኩ በተሽከርካሪ አደጋ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን የሕይወት መጥፋት ለመከላከል እና ለመቀነስ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዞኑ ሰፊ የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ከመሆን ባለፈ አገር አቋራጭ የትራንስፖርት መተላለፊያ መስመር በመሆኑ የትራፊክ አደጋው በዞኑ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል። መንግስት ችግሩን ለመቀነስ የተለያዩ መመሪያዎችና ደንቦችን እያወጣ ቢገኝም ለአሽከርካሪዎች ስነ ባህሪ መሻሻል የእምነት ተቋማትና ህብረተሰቡ ትምህርት እንዲሰጡ አሳስበዋል። "የተሽከርካሪ አደጋ እያደረሰ ባለው ጉዳት አምራች ዜጋና ወጣት ተመራማሪዎችን ከማጣት ባለፈ በሀገር እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ በመሆኑ ተባብረን ልንከላከለው ይገባል" ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ ቄስ በሻ ተሰማ ናቸው። አቶ ይልማ ሸዋ በበኩላቸው አንዳንድ አሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት በበቂ ሁኔታ ስልጠና የማይሰጡ ከመሆናቸው ባሻገር የመንግስት አካል ቁጥጥር ማነስ ለችግሩ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል። ከህግና መመሪያ ውጪ እንዲሁም ከትምህርትና እድሜ ደረጃ  በታች ሰልጣኞችን በሚቀበሉ የተሽከርካሪ ማሰልጠኛዎች መኖራቸውን የገለጹት ቄስ ባሻ መንግስት ተገቢ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። የዞኑ መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስዩም ዘሊባኖስ  በበኩላቸው እንደገለጹት በዚህ ዓመት 380 የትፊክ አደጋ የደረሰ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ31 ብልጫ አለው። በደረሰው አደጋ የ79 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና በ663 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቁመው 19 ሚሊዮን 841ሺህ ብር ግምት ያለው የንብረት ጉዳት መድረሱንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም