ቀጥታ፡

''ከኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ሕግና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚያስከብሩ ውሳኔዎች እንጠብቃለን''-የመቀሌ ከተማ ምሁራንና ባለሙያዎች

መቀሌ ሚያዚያ 8/2011 የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች አስተሳሰባቸውን አንድ በማድረግ የሀገሪቱ ሰላም እንዲጠበቅ መስማማት እንደሚጠበቅባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ 

ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ደስታ መኮንን እንዳለው የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች እርስ በርሳቸው ከመወነጃጀል ይልቅ ሀገሪቱ ከገባችበት የሰላም እጦት እንድትወጣ  የጋራ አቋም ያለው አስተሳሳብ ማራመድ  ይገባቸዋል።

ኢህአዴግ በጉባኤው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ያመለከተው ወጣቱ; የህዝብን ሰላም ለማምጣት ቁርጠኝነቱ በተግባር ማሳየት እንደሚጠበቅበት ገልጿል፡፡

በሃዋሳው የግንባሩ ጉባኤ ወቅት ያሳለፋቸው ውሳኔዎች  ተግባራዊነት በዝርዝር በመገምገም ጥንካሬውንና ድክመቱን ለይቶ የተሻለ ውሳኔ እንደሚያሳለፍ እምነት እንዳለው ተናግሯል፡፡

በሀገሪቱ የዜጎችመፈናቀል የሚታይበት ወቅት  መሆኑን የተናገረው  ወጣት ደስታ፤ አሁን ጉባኤው የችግሩ መንስኤ ከስር መሰረቱ በመገምገም የመፍትሄ እርምጃ ይወስዳል ብሎ እንደሚጠብቅ ገልጿል።

"የኢትዮጵያ ህዝብ አንዱ ድርጅት የለውጥ አካል ሌላው ድርጅት ደግሞ የፀረ ሰላም ኃይል ከማድረግ ይልቅ ኢህአዴግ እንደ አንድ ድርጅት ለህዝብ ያለውን ፋይዳ በማስቀመጥ ቁርጠኛ አቋም ሊኖረው ይገባል" ብሏል።

የአሁኑ ጉባኤ የተግባር  ይሆናል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ " ያለው ወጣቱ፣ የእህት ድርጅቶች እስካሁን የሄዱበት እርስ በርስ ከመጎዳዳት አስተሳሰብ ወጥተው የህግ የበላይነትን የሚከበርበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸው አመልክተዋል።

 ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ህዝብን ወደ አንድ አስተሳሰብ በማምጣት በተቀመጠው ፖሊስና ስትራቴጅ እንዲመራ የማድረግ ቁርጠኝነት ይዞ ለመስራት ራሱን ዝግጁ ማድረግ እንዳለበትም ወጣቱ አስተያየቱን ሰጥቷል።

በተለይ ምሁራን ኢህአዴግ ከገባበት ችግር እንዲወጣ ዘረኝነትና ልዩነት የሚያጎላ የጥላቻ ንግግሮችና ፅሁፎች ከመበተን ይልቅ ከመንግስት ጎን በመሆን የሀገሪቱን አንድነት ሊያስቀጥል የሚችል ሃሳብ  ማራመድ  እንዳለባቸውም መልዕክቱን አስተላልፋል

ሌላው የመቀሌ ነዋሪ አቶ ሰለሞን መሓሪ በበኩላቸው " የሀገር እድገት ለማስቀጠል ሰላም ወሳኝ በመሆኑ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የህዝብ  ሰላምና ደህንነት የሚያረጋግጥ ውሳኔ እንዲያስተላልፉ እጠብቃለሁ" ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርሱ በጥላቻ የሚተያይበት ድርጊት እንዲቆም የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች  ከጉባኤያቸው ተስማምተው  መውጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

"በአንድ ድርጅት ውስጥ የተለያዩ ሃሳቦች በማራመድሀገር ልትመራ አትችልም "ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ችግሩ ተፈትቶ ወደ ቀድሞ ቦታው እንደሚመለስ  ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በድርጅቶች መካከል በተፈጠረው ክፍተት  ወደ ግጭት መግባት እንደማይገባ ያመለከቱት ደግሞ  ሌላው አስተያየት ሰጪ   አቶ ገብሩ ካሕሳይ ናቸው።

"በመላ ሀገሪቱ  እየተከሰቱ ያሉት ችግሮች የሁሉም ኢትዮጵያውያን ችግር ናቸው "ያሉት አቶ ገብሩ፣ በኢትዮጵያውያን ደም የተገነባች ሀገር ማንም ሊያፈርሳት እንደማይችል የሚያመላክት  ውሳኔ  ከጉባኤው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

 የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች አስተሳሰባቸውን አንድ በማድረግ  ህዝቦች እንዳይጋጩ እና የሀገሪቱ ሰላም  እንዲጠበቅ መስማማት  እንደሚጠበቅባቸው አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም