ቀጥታ፡

ከኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር ውሳኔ እንሻለን--የአክሱም ነዋሪዎች

ሚያዝያ 8/2011 የአክሱም ነዋሪዎች በመካሄድ ላይ ያለው የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ዜጎቿ የትም ሰርተው የሚኖሩባት ኢትዮጵያን እንድትፈጠር የሚያደርግ ውሳኔ እንጠብቃለን አሉ።

ከግንባሩ አባል ድርጅቶች  የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር ውሳኔ እንደሚሹም  ገልጸዋል።

ከከተማው ነዋሪዎች አንዳንዶቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳመለከቱት ግንባሩ እያካሄደ ባለው ስብሰባ ዜጎች ያለአንዳች ችግር ተንቀሳቅሰው የሚኖሩባትና የሚሰሩባት አገር ለመፍጠር የሚያበቃ ውሳኔ ይጠብቃሉ።

ድርጅቱ በሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ዜጎች እንደልባቸው የትም ተንቀሳቅሰው ሰርተው የሚኖርባት ኢትዮጰያን ማየት እንደሚሹ የተናገሩት የአክሱም ዩኒቨርሲቲ መምህር ነጋሽ ኑርሁሴን ናቸው።

ስብሰባው የግንባሩ አባል ድርጅቶች በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ሞትና መፈናቀል ለማስቀረት የመሪነት ሚናቸውን በተግባር ለመጫወት ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት አጋጣሚ ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።

እንዲሁም የአገሪቱ ፌደራላዊ ሥርዓት ሳይሸራረፍ እንዲቀጥል ድርጅቱ ውሳኔ ያሳልፋል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ ብለዋል።

በአክሱም ከተማ የሓየሎም ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ግርማይ ካሕሳይ በበኩሉ በስብሰባው የሚሳተፉት አባል ድርጅቶች ከእልህና ከንትርክ ወጥተው የአገሪቱን ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፉ  እምነታቸውን ገልጸዋል።

‘‘ከኢህአዴግ የምክር ቤት ስብሰባ በአንዳንድ የኢትዮጰያ ክልሎች የሚታየውን ግድያ፣  መፈናቀልና የንብረት መውደም ሙሉ በሙሉ ለማስቆም የሚያስችል ጠንካራ ሕግና ሥርዓት ማየት እፈልጋለሁ‘‘ ያሉት ደግሞ በከተማው የሐየሎም ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ ኪሮስ ናቸው።

ከስብሰባው የአገሪቷ ኢኮኖሚ ዳግም እንዲያሰራራ ግንባሩ የመሪነት ሚና ለመጫወት መነሳታቸውን የሚገልጽ ውሳኔ እንደሚጠብቁም ተናግሯል።

ወጣት ዘርኡዳዊት አለማየሁ እንደተናገረው ምክር ቤቱ የሕገ ወጥ ጦር መሣሪያዎች ዝውውር ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግበትን ሁኔታ ይፈጥራል ብሎ ያምናል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ምክር ቤት ከትናንት ጀምሮ እያካሄደ ነው።

በአራት ብሔራዊ ድርጅቶች የተዋቀረው ግንባር በዚህ ዓመት መጨረሻ ሌሎች የብሄር ድርጅቶችን በማካተት አገር አቀፍ ፓርቲ ለመሆን እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም