ቀጥታ፡

አቶ ኢሳያስ ጅራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሰመራ ባካሄደው ስብሰባ አቶ ኢሳያስ ጅራን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ፡፡

ኦሮሚያ ክልልን የወከሉት አቶ ኢሳያስ ጅራ ዛሬ ማለዳ 66 ድምጽ በማግኘት አሸነፉ ቢባልም  ምርጫው ድጋሚ እንዲካሄድ ተወስኖ እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ በምርጫው መመሪያ መሰረት አቶ ኢሳያስ ከተሰጠው 145 ድምጽ አብላጫ ወይም 50 ሲደመር 1 ባለማግኘታቸው የፕሬዝዳንትነት ምርጫው ድጋሚ እንዲካሄድ የምርጫ አስመራጭ ኮሚቴው ወስኗል። ያገኙት ድምጽ ወደ መቶኛ ሲቀየር 46 ከመቶ በመሆኑ ምርጫው እንዲደገም ተደርጓል ነው የተባለው። በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ክልልን የወከሉት አቶ ኢሳያስ ጅራ በድጋሜ በተካሄደው ምርጫ ከተሰጠው 145 ድምጽ 87 ድምጽ በማግኘት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡ ሲሆን ፌዴሬሽኑን ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚመሩ ይሆናል። አማራ ክልልን የወከሉት አቶ ተካ አስፋው 58 ድምጽ አግኝተዋል። አቶ ኢሳያስ ከምርጫው በኋላ ለኢዜአ እንደገለጹት ምርጫው በጣም የተንዛዛ፣አሰልቺና የህግ ግድፈቶች የነበሩበት ነበር። ይህ የህግ ግድፈት ችግር በዛሬው ምርጫ ብቻ ሳይሆን ፌዴሬሽን ውስጥ ለረጅም ዓመታት የቆየ እንደሆነና ይህንንም ችግር በቀጣይ ለመቅረፍ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። እግር ኳሱን ለማሳደግ በታዳጊና ወጣት እግር ኳስ ፕሮጀክቶች ላይ በመስራት ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሰፍን ለማድረግ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እሰራለሁ ብለዋል። የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠርም ከዛሬ ጀምሮ ከጅማ አባጅፋር ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅነታቸው እንደለቀቁም አሳውቀዋል። የትግራይ ክልልን የወከሉት አቶ ተስፋዬ ካህሳይና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን የወከሉት አቶ ጁነዲን ባሻህ በድጋሚ ከተካሄደው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸው የሚታወስ ነው። ወለጋ የተወለዱት አቶ ኢሳያስ ጅራ ከዚህ ቀደም የሰበታ ከተማ ክለብ ሥራ አስኪያጅ የነበሩ ሲሆን ለ22 አመታት በስፖርቱ በአመራርነት አገልግለዋል። ፕሬዝዳንቱ የኦሮሚያን ክልል ወክለው ማሸነፋቸውን ተከትሎ ኦሮሚያ በኮሚቴው ምርጫ እጩ ማወዳደር ስለማይችል ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባልነት 10 ሰዎች የሚመረጡ ይሆናል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ  ከዚህ በፊት አራት ጊዜ መራዘሙ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም