የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው 70 በመቶ ወጭ የሚወጣው በፕሮጀክቶች ዝግጅት ወቅት መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው 70 በመቶ ወጭ የሚወጣው በፕሮጀክቶች ዝግጅት ወቅት መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 8/2011 በኢትዮጵያ የኮንስትራከሽን ኢንዱስትሪው የገንዘብ ብክነት 70 በመቶ የሚሆነው በፕሮጀክት ዝግጅት ምዕራፍ ወቅት የሚከሰት መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት ብቻ በግንባታ ላይ ከነበሩ የመንግስት ሜጋ ፕሮጀክቶች ከ 43 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ወጭ ማውጣቷን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የግዥ ስርዓት መጓተት፣ የዲዛይን መቀያየር፣ የፕሮጀክቶች አያያዝና ክትትል ደካማ መሆን ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ የአማካሪዎች፣ ተቋራጮችና ግብዓት አቅራቢዎች የተቀናጀ አሰራረ አለመከተል ደግሞ የዘርፉ ፈተናዎች ናቸው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አስመሮም ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኮንስትራከሽን ኢንዱስትሪው ከሚደርሰው ብክነት 70 በመቶ የሚሆነው በፕሮጀክት ዝግጅት ምዕራፍ ወቅት የሚፈጸም ነው።
በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተጨማሪ የገንዘብ ወጪ፣ ከእቅድ በላይ ጊዜና የጥራት መጓደል ዛሬም አብረው ያሉ የእድገታችን ጎታች ችግሮች መሆናቸውም ተገልጿል።
ኢንስቱትዩቱ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ከፍተኛ የኮንትራት ዋጋ ባላቸው 52 የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች ላይ በተጠና ጥናት በአብዛኛው ተጨማሪ የገንዘብና የጊዜ ወጭ የሚከሰተው በፕሮጀክት ዝግጅት ሂደት ወቅት መሆኑን ደርሰንበታል ብለዋል።
በጥናቱ የተካተቱት 10 የውሃ፣ 10 የህንፃ እና 32 የመንገድ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን የገለጹት ኢንጂነር አስመሮም፤ ጠቅላላ ዋጋቸው ከ 37 ቢሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።
በፕሮጀክት ዝግጅት ወቅት ማለትም በቅድመ አዋጭነት ጥናት፣ በዲዛይን ዝግጅት ሂደት፣ በጨረታ ሰነድ ዝግጅት፣ በግዥ አካሄድ ትክክለኛ አቅራቢ በመምረጥ ሂደት የሚከሰቱ ጉደለቶች ደግሞ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ጥናት ከተደረገባቸው 52 የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች 76 በመቶ ተጨማሪ ወጭ ማስወጣታቸውን ገልጸው፤ ከዚህም 70 በመቶ የሚሆነው በፕሮጀክት ዝግጅት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራዊ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ጥራት ማረጋገጫ ያለው ዘመናዊ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት የልህቀት ማዕከል ለመገንባት ከ 2008 ዓ.ም ጀምሮ ሂደት ላይ ናቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም የኮንስትራከሽን ዘርፉን የሚያዘምኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች የሚከናወኑበት እንዲሁም የሰው ሃይል አቅም የሚጎለብትበት ማዕከል መሆኑንም ገልጸዋል።