ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰሊጥ በማምረት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው

ጎንደር ግንቦት 26/2010 በአማራ ክልል በ2010/11 ምርት ዘመን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰሊጥ በማምረት ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡ በሰሊጥ ምርትና ግብይት ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ  ተጀምሯል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የቢሮው ኃላፊ አቶ ፍሰሃ ወልደሰንበት እንደተናገሩት በክልሉ ከፍተኛ ሰሊጥ አምራች በሆኑት በምእራብና ማእከላዊ ጎንደር ዞኖች 273 ሺህ ሄክታር መሬት በሰሊጥ ለመሸፈን ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ በምርት ዘመኑ ሰሊጥን በመስመር በመዝራት፣ ማዳበሪያና የተሻሻሉ የሰሊጥ ዝርያዎችን አርሶአደሩና ባለሀብቱ በስፋት እንዲጠቀም በማድረግ የሰሊጥ ምርታማነትን በሄክታር ከሚገኘው 4 ኩንታል ወደ 8 ኩንታል ለማሳደግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው፡፡ በክልሉ ሰሊጥ አብቃይ አካባቢዎች በልማቱ የተሰማሩ ባለሀብቶችና አርሶአደሮች በምርምር የወጡ፣ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ረገድ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ለሰሊጥ ምርታማነት ማነቆ የሆኑ ልማዳዊ የግብርና አሰራሮችን በመቀየርና የዘርፉን ምርታማነት በመጨመር የሰሊጥ ኤክስፖርትን ማሳደግ እንዲቻል ግብረሃይል ተቋቁሞ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለውጪ ገበያ ከሚላከው የሰሊጥ ምርት 49 በመቶ ይሸፍናል ያሉት ኃላፊው ባላፈው አመት ብቻ ከክልሉ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ሰሊጥ ለገበያ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው አመት ከክልሉ ለውጪ ገበያ ከቀረበው የሰሊጥ ምርት 166 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ስለመገኘቱም በምክክር መድረኩ በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ ተመልክቷል፡፡ የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል የሰብል ተመራማሪ አቶ አስፋው አዛናው ማእከሉ የሰሊጥን ምርታማነት ለማሳደግ ባለፈው አመት በምርምር የተገኘ ጎንደር 1 የተባለው የሰሊጥ ዝርያ በሄክታር ከ8 እስከ 10 ኩንታል ምርት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሰሊጥ ዝርያው አርሶአደሩና ባለሀብቱ ከሚጠቀሙበት የአካባቢ ዝርያ ጋር ሲነጻጸር ከአራት እስከ ስድስት ኩንታል የሚደርስ የምርት ጭማሪ ማስገኘቱን በአርሶአደሩ ማሳ ተሞክሮ መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡ ማእከሉ ባለፈው አመት ለሙከራ ስራ ላይ የዋለው ሰሊጥና ማዳበሪያን መጥኖ በመሰመር የሚዘራው ዘመናዊ ማሽን በሄክታር የ2 ኩንታል የምርት ጭማሪ አስገኝቷል፡፡ በ2010/11 ምርት ዘመን 18ሺ አርሶአደሮችና ባለሃብቶች ቴክኖሎጂውን በስፋት እንዲጠቀሙ ለማድረግ በማእከሉ እቅድ መያዙንም ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ሰሊጥ አብቃይ በሆኑት በምእራብና ማእከላዊ ጎንደር ዞኖች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያወጡ 1ሺ 154 ባለሀብቶች እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ የገጠር መሬት ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ በላይ ናቸው፡፡ ባለሀብቶቹ 134ሺ 218 ሄክታር መሬት በውላቸው መሰረት ተረክበው ሰሊጥና ጥጥ በየአመቱ በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮ የመኸር ወቅት 400 ሄክታር መሬታቸውን አዳዲስ የግብርና አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር ሰሊጥ ለመዝራት መዘጋጀታቸውን የገለጹት በምእራብ አርማጭሆ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ሙሉአለም ምልምሌ ናቸው፡፡ 1ሺ 800 ሄክታር መሬት በየአመቱ ለሰሊጥ ልማት  እንደሚያውሉ የተናገሩት አቶ መልካሙ አብረሃ የተባሉት ባለሀብት በበኩላቸው ''ከዚህ ቀደም በሄክታር ሳገኝ የቆየሁትን 4 ኩንታል ወደ 6 ኩንታል ለማድረስ አቅጃለሁ'' ብለዋል፡፡ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ መጠቀም የሰሊጥ ምርታማነት እንደሚጨምር በተግባር አረጋግጫለሁ የሚሉት አቶ መልካሙ ሰሊጥን በመስመር በመዝራት ጭምር በቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብርና ስራ ለማካሄድ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ ላይ በምእራብና ማእከላዊ ጎንደር ዞኖች በሰሊጥ ልማት የተሰማሩ ከ1ሺ በላይ ባለሀብቶች አርሶአደሮች የግብርና ባለሙያዎችን ጨምሮ የክልልና የዞን አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም