ቀጥታ፡

በጋምቤላ ማረሚያ ቤት በተነሳ ግጭት 92 ታራሚዎች አመለጡ

ጋምቤላ ሚያዚያ 7/2011 በጋምቤላ ከተማ ዙሪያ ዞን ማረሚያ ቤት ከተፈጠረው የእርስ በእርስ ግጭት ጋር ተያይዞ 92 ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች አምልጠው መውጣታቸውን ማረሚያ ቤቱ አስታወቀ።

ማረሚያ ቤቱ የወጡት ታራሚዎች ላይ ክትትል እያደረገ መሆኑን አስታውቋል ።  

የዞኑ ማረሚያ ቤት አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር ጆን ኡሞድ ለአዜአ  እንደገለጹት በውሃ ምክንያት በሁለት ግለሰቦች  መካከል የተነሳ አለመግባባት ሰፍቶ ወደ ግጭት በማምራቱ ከ316 ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች መካከል 92ቱ አምልጠው ወጥተዋል።

ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች ሊያመልጡ የቻሉት በወቅቱ በማረሚያ ቤቱ በቂ  የፖሊስ ኃይል ስላልነበረ መሆኑን ገልጸው በግጭቱ በሶስት ሰዎች ላይ ከደረሰው መጠነኛ መቁሰል በስተቀር በህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከፌዴራልና ከክልል የፀጥታ አካላት አስፈላጊው ኃይል ተጨምሮ የማረጋጋት ስራ በመከናወኑ የተሻለ ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተው ከማረሚያ ቤቱ  ባመለጡ ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች ላይ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝምጠቁመዋል።

የኢዜአ ሪፖረተር ከስዓት በኋላ በቦታው በመገኘት ባደረገው ምልከታ በማረሚያ ቤቱ የተረጋጋ ሁኔታ እንዳለ ታዝቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም