ቀጥታ፡

ለትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ስርዓተ ትምህርት እንደሚዘጋጅ ተጠቆመ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 7/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የከተማ ትራንስፖርት ስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማዘመንና በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ያስችላል የተባለውን ስርዓተ ትምህርት ለማዘጋጀት የሚያስችል "የከተማ ትራንስፖርት ስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ጥናት" በማካሄድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተወያየ ነው።

ዛሬ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ከነባር ሰባት ዩኒቨርስቲዎች ተወካዮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የተካሄደው ውይይት የትራንስፖርት አገልግሎትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት ስርዓተ ትምህርት ለመቅረጽ የሚያስችል ምክረ ሀሳብ ለማግኘት ያግዛል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር  ሰመረ ጀላሉ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለል የሚያስችል ስልጠና ለመስጠት ስርዓተ ትምህርት ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ጽህፈት ቤቱ ከዩኒቨርስቲዎችና ከባለድርሻ አካላት የተገኘውን ምክረ ሀሳብ ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርብ ታውቋል።

ጽህፈት ቤት በመዲናዋ ብቁ የሰው ኃይሉን በማፍራትና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመተግበር በ2016 ዓ.ም አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ወጪ ቆጣቢ የከተማ የትራንስፖርት ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም