የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥበት ቅርጫፍ ከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥበት ቅርጫፍ ከፈተ
ሚያዝያ 07 /2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴት ሰራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡበትን አዲስ ቅርንጫፍ በአዲስ አበባ ቦሌ አትላስ አካባቢ ከፍቷል።
አዲስ የተከፈተው ቅርንጫፍ በቀድሞው የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ለይኩን ብርሃኑ የተሰየመ ሲሆን 1 ሺህ 400ኛው የባንኩ ቅርንጫፍ ሆኖ በዛሬው እለት ተመርቆ ስራ ጀምሯል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና እንደገለጹት፤ሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡበት ቅርጫፍ የተከፈተው ሴቶች ለአገር እድገት ላላቸው አበርክቶ እውቅና ለመስጠት ነው።
‘’በአገልግለቱ የጾታ እኩልነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተገንዘበናል’’ ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይም በዋና ዋና ከተሞች ሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡባቸው ቅርጫፎች ይከፈታሉ ብለዋል።
የኀብረተቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አገልግሎቶችን ጥናት በማድረግ እየተተገበሩ ሲሆን የሴቶች፣የወጣቶች ፣የትምህርት የቁጠባ ሂሳቦችና ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ይገኙበታል።
ከአምስት ዓመታት በፊት የሴቶች የቁጠባ ሂሳብ አገልግሎት እንደተጀመረ ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ ቆጣቢዎች ከመደበኛ የቁጠባ ሂሳብ የተሻለ ወለድ የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቱን አንስተዋል።
ከባንኩ ጋር ዕቃ አቅራቢዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ግብይት ሲፈጽሙ ቅናሽ እንዲያገኙ ማበረታቻዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሴቶች የቁጠባ አገልግሎት ከ34 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸው ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ሴት ደንቦችን ማፍራት መቻሉንም ተናግረዋል።
የባንኩ የቀድሞ ፕሬዝዳንትና አዲሱ ቅርንጫፍ የተሰየመላቸው አቶ ለይኩን ብርሃኑ በባንኩ በነበራቸው ቆይታ ላበረከቱት አስተዋጾኦ ባንኩ እውቅና መስጠቱን አመስግነዋል።
ለሴቶች ሙሉ ኃላፊነት መስጠት በራስ መተማመናቸው እንደሚገነባ የገለጹት አቶ ለይኩን ይህም ለአገር የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
አቶ ለይኩን ብርሃኑ ላለፉት 42 ዓመታት በተለያዩ የግልና የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት አገልግለዋል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን አዲስ አበባ ባንክ በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉ ሲሆን የኢትዮያ ንግድ ባንክን በአብዮቱ ግዜ የመሩ አንጋፋ ባለሙያ ናቸው።