በቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ወልቂጤ ከተማና ሃዋሳ ከተማ አሸነፉ - ኢዜአ አማርኛ
በቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ወልቂጤ ከተማና ሃዋሳ ከተማ አሸነፉ
አዲስ አበባ ግንቦት 26/2010 ስምንት ቡድኖች በሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በተደረጉ የሁለተኛ ዙር አምስተኛ ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማና ሃዋሳ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል። በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርትና ወልቂጤ ከተማ እያደረጉት የነበረው ጨዋታ ወልቂጤ 48 ለ 44 በሆነ ውጤት እየመራ በጣለው ከባድ ዝናብ ተቋርጦ ነበር። 1 ደቂቃ ከ25 ሰከንድ ጨዋታው እየቀረው የተቋረጠው ጨዋታ በራስ ሃይሉ ጅምናዚየም እንዲካሄድ ተደርጎ ወልቂጤ ከተማ 51 ለ 46 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጣም ተመጣጣኝና የተመልካችን ቀልብ የሳበ ሲሆን ብዛት ያላቸው የወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ታይቷል። በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ይደረጋል ተብሎ የነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የሃዋሳ ከተማ ጨዋታ በጣለው ከባድ ዝናብ በራስ ኃይሉ ጅምናዚየም እንዲካሄድ የተደረገ ሲሆን በውጤቱም ሃዋሳ ከተማ 35 ለ 29 አሸንፏል። የሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በባህርዳር የአማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይንና ጎንደር ከተማ ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ መርሃ ግብር ወጥቶላቸው ነበር። ነገር ግን አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ሜዳና የማወዳደሪያ ቁሳቁሶቹን እንዲያሟሉ ቢጠየቁም ባለሟሟላታቸውና ውድድሩ እንዲራዘም መርሃ ግብሩ ከወጣ በኋላ ምንም አይነት ጥያቄ ለኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ያላቀረቡ በመሆኑ የጨዋታው ኮሚሽነር የጎንደር ከተማ በውድድሩ ደንብ መሠረት በፎርፌ አሸናፊ እንዲሆን መወሰኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና ከምባታ ዱራሜ በፎርፌ አሸንፈዋል። ትናንት ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከቡታጅራ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ቡታጅራ ከተማ ሜዳ ባለመገኘቱ ከምባታ ዱራሜ በፎርፌ አሸናፊ መሆን ችሏል። በተመሳሳይ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ድሬዳዋ ባለመገኘቱ ኮልፌ የፎርፌ አሸናፊ እንዲሆን መወሰኑን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ትናንት በከባድ ዝናብ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የቂርቆስ ክፍለ ከተማና የፌደራል ፖሊስ ጨዋታ ዛሬ የተካሄደ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ 23 ለ 21 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በዝናብ 22ኛው ደቂቃ ላይ ከመቋረጡ በፊት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ 7 ለ 4 በሆነ ውጤት እየመራ ነበር። በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 9 ቡድኖች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።